Wednesday 31 May 2017

የህወሃት መሪዎች የትግራይ ተወላጅ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ በአለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በሃላፊነት እንዲሰራ ድጋፍ እንደማያደርጉ ተገለጸ

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስልጣኑን የያዙት የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት መሪዎች የትግራይ ተወላጅ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ በአለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በሃላፊነት እንዲሰራ ድጋፍ እንደማያደርጉ አንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ገለጹ።
በአፍሪካ ልማት ባንክ እስከ ምክትል ፕሬዚደንትነት ለ15 አመታት ያገለገሉት አንጋፋው ኢትዮጵያዊ አቶ ተካልኝ ገዳሙ “Republican on the Throne” በተባለውና ከአመታት በፊት ለንባብ ባቀረቡት መጽሃፋቸው እንደገለጹት ለአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚደንትነት ሳይወዳደሩ የቀሩት የኢትዮጵያ መንግስት የድጋፍ ወረቀት ስለነፈጋቸው መሆኑን አውስተዋል።
ይህ በእርሳቸው እንዳልተጀመረና ከርሳቸው በፊትም በሌሎች የትግራይ ተወላጆች ባልሆኑ ኢትዮጵያውያን ላይ ተፈጻሚ መሆኑንም በመጽሃፋቸው ያመለከቱ ሲሆን፣ ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ ይህንኑ በዝርዝር ተመልክተዋል።
የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን በአሜሪካ ኤሊኖይና በስመጥሩ ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ካጠናቀቁ በኋላ፣ በኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት ሰራተኛ በመሆን ስራ የጀመሩት አንጋፋው ኢትዮጵያዊ አቶ ተካልኝ ገዳሙ፣ ከቀዳማዊ ሃ/ስላሴ ዘመን በመጨረሻና በደርግ ዘመን በሚኒስትርነት ሃገራቸውን አገልግለዋል።
በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን በመልቀቅ ወደ አቢጃን ኮትዲቪዋር በማምራት በአፍሪካ ልማት ባንክ እስከምክትል ፕሬዚደንትነት 15 አመታት ያልገለገሉት አቶ ተካልኝ ገዳሙ፣ በቦታው ባሳዩት ውጤታማነት ለፕሬዚደንትነት እንዲወዳደሩ ከተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮች ግፊት ቢደረግም፣ በኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ባለማግኘታቸው ሳይሳካ መቅረቱን ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ አስታውሰዋል።
አቶ ተካልኝ ገዳሙ በመጽሃፋቸው እንዳመለከቱት የትግራይ ተወላጆች ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን በአለም አቀፍ መድረክ ስፍራ እንዳያገኙ ድጋፍ መንፈግ የተጀመረው በርሳቸው እንዳልሆነና ሌሎች አብነቶችን ጠቅሰዋል።
አቶ ተፈራ ራስወርቅ የተባበሩት መንግስታት አካል ለሆነው ኢንተርናሽናል ቴሌኮሚኒኬንሽን ዩኒየን እንዳይወዳደሩ በመንግስት ድጋፍ መነፈጋቸውን አስታውሰው፣ አቶ ይልማ ታደሰም ለአፍሪካ ህብረት ያደርጉት የነበረውን ውድድርም በተመሳሳይ በመንግስት ለዜጎቹ በነፈገው ድጋፍ መስተጓጎሉም አመልክተዋል።
ስልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት የትግራይ ተወላጅና የህወሃት አባል የሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለአለም አቀፍ የጤና ድርጅት እንዲወዳደሩ ድጋፍ ከመስጠት ባሻገር የቅስቀሳ ስራ እንዲሰሩ ከ60 በሚበልጡ ሃገራት እንዲንቀሳቀሱ ሁኔታዎችን አመቻተዋል።
ምርጫው በተካሄደበት ጀኔቫም የመንግስት ልዑካንን የላከ ሲሆን፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ አሸንፈው ወደ ሃገር ቤት ሲመለሱም የጀግና አቀባበል አድርጎላቸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች በተዘጋጀው መድረክ ላይም ተገኝተው ደማቅ መስተንግዶ ተደርጎላቸዋል። የትግራይ ወጣቶችም የአቶ መለስና የዶ/ር ቴዎድሮስን አርዓያ እንዲሚከተሉ ገልጸዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ሆነው መመረጣቸውን በተመለከተም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊነትን ስልጣን የያዙ ያህል እየተጋነነ ይገኛል።የዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ስልጣን ከተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊነት ጋር በማነጻጸር እንዲመለከቱ ኢሳት ያነጋገራቸው በጄኔቭ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ዶ/ር ካሳ ከበደ ልዩነቱን በአንድ ከተማ ከንቲባና በከተማው ውስጥ በሚኖር አንድ ሃኪም ቤት ሃላፊ ጋር አነጻጽረውታል።

ምንጭ:ኢሳት 

Monday 22 May 2017

አርበኞች ግንቦት 7 ቴድሮስ አድሃኖምን የሚያጋልጥ መረጃ ለቀቀ

የዓለም ጤና ጥበቃ ዳይሬክተርነት በህዝባችን ላይ የተፈጸመውን ወንጀል መሸፈኛ ሊሆን አይችልም!

አርበኞች ግንቦት 7

ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ድርጅትና እንደ መንግሥት በአገራችን ውስጥ እንዲተገበሩ በወጡ አፋኝ ፖሊሲዎችና በህዝባችን ላይ በተወሰዱ ፋሽስታዊ እርምጃዎች ሁሉ ወሳኝ ሚና ከነበራቸው ጥቂት የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች መካከል ቴዎድሮስ አድሃኖም አንዱ ነው።

ይህ ወንጀለኛ ግለሰብ የአምባገነኖች ስብስብ በሆነው የአፍሪካ ህብረት ሙሉ ድጋፍ አግኝቶ ለአለም ጤና ጥበቃ ዳይሬክተርነት እጩ ሆኖ ሲወጣ እንደ ትልቅ ገድል የተቆጠረለት የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ሆኖ ባገለገለባቸው አመታት አስመዝግቧል የተባለው የጤና መሻሻልና በውጪ ጉዳይ ሚንስትርነት አበርክቷል የተባሉት አስተዋጾዎች ናቸው።
ምዕራባዊያን ለጋሾች ለታዳጊ አገራት የጤና አገልግሎት በየአመቱ የሚሰጡትን ገንዘብ የሚመድበውና የመደበውን ገንዘብ ሥራ ላይ መዋሉን የመከታተል ሃላፊነት የተጣለበት ግሎባል ፈንድ የተባለው አለም አቀፍ ተቋም ቴዎድሮስ አድሃኖም የአገራችንን ጤና ጥበቃ ሚንስትር መሥሪያ ቤት በመራበት ወቅት ለነፍስ አድን ዕርዳታ ከሰጠው አንድ ቢሊዮን ሶስት መቶ ስድስ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ውስጥ ከፍተኛውን ገንዘብ እንዴት አድርጎ እንዳባከነና ለፖለቲካ ፍጆታ እንደዋለ በኦዲተሮቹ አስመርምሮ ይፋ አድርጓል።

ሜይ 14 ቀን 2012 ዓም ይፋ የሆነው ይህ የምርመራ ሪፖርት እንደሚያትተው በፈረንጆች አቆጣጠር 2009 እና 2010 ለአገራችን የተሰጠው የነፍስ አድን እርዳታ ገንዘብ ዋና አላማው በደማቸው ውስጥ የኤች አይቪ ቫይረስ የተገኘ ፤ በሳምባ ህመምና በወባ የተጠቁ ሰዎችን ህይወት ከሞት ለማትረፍ የታሰበና የገንዘብ ድልድሉም የሚከተለውን የሚመስል ነበር።

• ለሳምባና ወባ ህክምና 404 ሚሊዮን ዶላር
• ለኤች አይቪ 879 ሚሊዮን ዶላር
• የኤች አይቪ ተሸካሚዎች ኔት ዎርክ 9 ሚሊዮን ዶላር
• በኤች አይቪ በሽታ ወላጆቻቸውን ላጡ ህጻናት መርጃ 14 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ አንድ ነጥብ ሶስት መቶ ስድስት ሚሊዮን ዶላር

ከዜጎች ህይወትና ደህንነት በላይ የፖለቲካ ሥልጣን ዕድሜው እጅግ የሚያሳስበው የህወሃቱ ቴዎድሮስ አድሃኖም ግን ለነፍሰ አድን ከተሰጠው ከዚህ መጠነ ሰፊ ገንዘብ ውስጥ 165,393,027 /አንድ መቶ ስልሳ አምስት ሚሊዮን ሶስተ መቶ ዘጠና ሶስት ሺ ሃያ ሰባት/ የአሜሪካን ዶላር የለተቋሙ እውቅናና ፈቃድ 1309 ጣቢያዎችን አስገንብቻለሁ በማለት ገንዘቡን እንዳባከነ የግሎባል ፈንድ ኦዲተሮች ባደረጉት ምርመራ ደርሰውበታል። ከዚህም በተጨማሪ 57, 851, 941 ዶላር የት እንደገባ ማረጋገጫ አልተገኘለትም ።

የት እንደገባ ማረጋገጫ አልተገኘለትም የተባለውን ሃምሳ ሰባት ሚሊዮን ስምንት መቶ ሃምሳ አንድ ሺ ዘጠኝ መቶ አርባ አንድ ዶላር ጉዳይ የሚያውቀው ቴዎድሮስ አድሃኖም ብቻ ሊሆን እንደሚችል ገምተን ወደ ጎን እንተወውና በእርዳታ ገንዘቡ ተገንብተዋል ስለተባሉት ጤና ጣቢያዎች ሪፖርቱ የሚያወራውን እንመልከት ። በግሎባል ፈንድ የኦዲት ሪፖርት መሠረት ቴዎድሮስ አድሃኖም 1309 ጤና ጣቢያዎችን በተቋሙ ገንዘብ ገንብተናል ብሏል።
ከነዚህ 1309 ጤና ጣቢያዎች ውስጥ የግሎባል ፈንድ ኦዲተሮች 77ቱን እንዲጎበኝ ተደርጎ፤

• 71%ቱ ለጤና ጣቢያ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ውስጥ አንዱ የሆነውን የውሃ አገልግሎት በጭራሽ እንደሌለው፤
• 32%ቱ ሽንት ቤት የሚባል ነገር እንዳልተሠራለት፤
• 53%ቱ ገና ተሠርተው ከማለቃቸው የህንጻዎች ወለሎች በከፍተኛ ሁኔታ ተሰነጣጥቀው መገኘታቸውን፤
• 19%ቱ ደግሞ ጣራቸው ማፍሰስ መጀመራቸውን አረጋግጦአል።

የወያኔን ባለሥልጣናት የሞራልና የሙስና ዝቅጠት ደረጃ ግምት ውስጥ አስገብተን ይህንን የኦዲት ሪፖርት ማንበብ ከፈለግን እነዚህ ለጉብኝት ክፍት የሆኑት 77 ጣቢያዎች በተሻለ የጥራት ደረጃ ላይ ይገኛሉ ተብለው የተገመቱና በዚህም የተነሳ ቢጎበኙ ለጋሾች ተጨማሪ ዕርዳታ ሊሰጡን ይችላሉ አለያም ደግሞ በተሠራው ሥራ ያወድሱናል በሚል እምነት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ለጉብኝት ክፍት ያልነበሩት ቀሪዎቹ 1232 ህንጻዎች በምን ሁኔታ ላይ ሊገኙ እንደሚችሉ ከዚህ በመነሳት ማወቅ ይቻላል። ጭራሽ የመሠረት ድንጋይ ሳይጣል ተሠርተዋል ተብለው ሪፖርቱ ውስጥ የተጠቃለሉ ሊኖሩ እንደሚችልም መጠርጠር አይከፋም ። የኛ ነው የሚሉትን የትግራይ ህዝብ ነፍስ ለመታደግ በዚያ በ1977ቱ የድርቅ ወቅት ከአለም ለጋሾች የተላከን የዕርዳታ እህል ሽጠው በምትኩ አሸዋ በጆንያ ሞልተው ሂሳብ ያወራረዱ ሽፍቶች የፈረንጅ እግር በማይደርስባቸው የአገሪቱ ክፍሎች የጤና ጣቢያ ህንጻዎችን አስገንብተናል ብለው ገንዘቡን ቢበሉት ምን ያስገርማል?

የግሎባል ፋንድ ኦዲት ሪፖርት ከላይ በተገለጸው ብቻ አላቆመም ። ድርጅቱ ለነፍስ አድን በሰጠው ገንዘብ ህክምና እርዳታ ይሰጥባቸዋል የተባሉና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ 46 የህክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ጎብኝተው አብዛኛዎቹ የቧንቧ ውሃ አገልግሎት እንደሌላቸው፤ ለበሽታ ናሙና ምርመራ የሚጠቀሙባቸው ማይክሮስኮፖች የተበላሹና ያረጁ በመሆናቸው በተለይ የወባና የሳምባ በሽታን በትክክል ለመለየት የማያስችሉ መሆናቸውን ፤ በ46ቱም ተቋማት ውስጥ ካሉ ዶክተሮችና ነርሶች ስለወባ በሽታ ማኔጅመንት አንዳቸውም ሥልጠና አግኝተው እንደማያውቁ፤ ለህመምተኞች የሚሰጠው መድሃኒት መበላሸት ወይም አለመበላሸቱ በወቅቱ ቁጥጥር እንደማይደረግበት ወዘተ መታዘባቸውን አጋልጠዋል።

የኢትዮጵያዊያንን ህይወት ለማትረፍ ግሎባል ፈንድ የሰጠው ገንዘብ በዚህ መልኩ መባከኑንና በእርዳታ ስምምነቱ ውስጥ ላልተገለጸ አላማና ተግባር መዋሉን ካረጋገጠ ቦኋላ ተቋሙ እርምጃ ለመውሰድ የጀመረውን እንቅስቃሴ በወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር የነበረው ሟቹ መለስ ዜናዊ ጣልቃ ገብቶ እንዳከላከለና ለግሎባል ፈንድ የገንዘብ ዕርዳታ ከሚለግሱ የአለም ዲታዎች አንዳንዶቹ የተለያየ ግፊት ፈጥረው ተድበስብሶ እንዲቀር እንዳደረጉት የሚያጋልጥ መረጃ በእጃችን አለ።

እንግዲህ ቴዎድሮስ አድሃኖም የጤና አገልግሎቶችን አስፋፍቶአል በማለት ለአለም ጤና ጥበቃ ዳይሬክተርነት እያደረገ ባለው ዘመቻ በመናፈስ ላይ ካለው የፈጠራ ህይወት ታሪክ በስተጀርባ ያለው እውነታ ይህ እንደሆነ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እናውቃለን። በዚህ ዘረፋ ምክንያት ህክምና አጥተው ህይወታቸው የተቀጠፈ ዜጎች ቁጥርም ውሎ አድሮ ጊዜ የሚያጋልጠው ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

ከዚህ ወንጀል በተጨማሪ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሆኖ ባገለገለባቸው ጊዜያትም፡ ድርጅቱ ህወሃት በህዝባችን ላይ የፈጸማቸውን የጎዳና ላይ ጭፍጨፋዎች ፤ በየእስር ቤቱ በተወረወሩ የፖለቲካ እስረኞች ላይ የደረሰውን ሰቆቃና ግርፋት ፤ እንዲሁም እትብታቸው ከተቀበረበት ቦታ በጉልበት እንዲፈናቀሉ ተደርገው ለጎዳና ተዳዳሪነት የተዳረጉ በሺዎች የሚቆጠር ዜጎች ስቃይና መከራ ተሸፍኖ እንዲቀር የቻለውን ሁሉ አስተዋጾ አድርጎአል። የንቅናቄያችን ዋና ጸሃፊ የሆነውን ጓዳችን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ከየመን አየር ማረፊያ አሳፍኖ በመውሰድ ተግባር ውስጥም እጁ እንዳለበት እናውቃለን። የአጋዚ ጦር በቅርቡ በኢሬቻ በአል ላይ፤ በጎንደር፤ በባህርዳር ፤ በጌዶ ወዘተ የፈጸመውን ፋሽስታዊ ጭፍጨፋ ጀማሪ ዲሞክራሲ ስለሆን ህግ አስከባሪዎች በእውቀት ማነስ የፈጸሙት ነው በማለት እያናናቀ በተለያዩ አለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተዘባብቶብናል።

እንዲህ አይነት ወንጀለኛን የአፍሪካ አምባገነኖችና አንዳንድ ለሰው ልጆች ሰብዓዊ መብት ደንታ የሌላቸው የአገራቸውን ጥቅም ብቻ ለማስከበር ደፋ ቀና የሚሉ ምዕራባዊያን መንግሥታት አሞጋግሰው ለአለም ጤና ጥበቃ ዳይሬክተርነት ቦታ ቢያነግሱትም ባያነግሱትም ፍትህ እኩልነትና ነጻነት በምድራች ኢትዮጵያ እውን በሚሆንበት ቀን በግልና በቡድን ከፈጸመብን ወንጀል ተጠያቂነት ሊያድኑት እንደማይችሉ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል።
የተባበሩት መንግሥታት አካል የሆነው የአለም ጤና ጥበቃ ድርጅት በእስከዛሬ ታሪኩ በሙያቸውና በሥነምግባራቸው የላቁ ሰዎችን እንጂ እንደ ቴዎድሮስ አድሃኖም ያሉ በሙያቸው የቀጨጩ ፤ ለፖለቲካ ፓርቲያቸው የሥልጣን ዕድሜ መራዘም ሲሉ ንጹሃንን በጠራራ ጸሃይ በማስጨፍጨፍ በሰው ደም የተጨማለቁ ወንጀለኞችን አስተናግዶ አያውቅም። ለንግዳቸው እንጂ ለጥቁር ህዝቦች ህይወት ደንታ የሌላቸው አለም አቀፍ ቱጃሮች እንደ ቴዎድሮስ አድሃኖም አይነት በጥቅም የሚገዛ ታዛዥ ሎሌ በቦታው ለማስቀመጥ እያደረጉ ያሉትን ሩጫ በቅርበት የሚከታተለው አርበኞች ግንቦት 7 የአለም ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት የወንጀለኞች መደበቂያ ዋሻ ሊሆን እንደማይችል ይገነዘቡት ዘንድ ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ

Tuesday 2 May 2017

ቀላል የስነልቦና ጦርነት ስልቶች: ማግለል፣ ማድነቅ እና ማብራራት

ማግለል - የህወሓት፣ የብአዴን፣ የኦህዴድና የደኢህዴን እንዲሁ የአጋር ድርጅቶች ቀንደኛ አባላትን፤ ግፈኛ የፌደራል ፓሊስ አባላትን፣ በየመንደሩ እያነፈነፉ ያሉት ጆሮ ጠቢዎችን፣ ጭንቅላት የለሽ ፓሊሶችን፣ ፍርደ ገምድል ዳኞችን፣ ሀሰተኛ አቃቢያነ ህግ፣ ካድሬ መምህራንን፣ የመንደር ለፍላፊ ውሸታም ካድሬዎችን፣ አድርባይ “አርቲስቶችን”፣ “ልማታዊ ጋዜጠኞችን” ማግለል፣ መጠየፍ፣ ማራቅ፣ መናቅ፣ ማዋረድ፤ በእነሱ ላይ ማፌዝ፤ ድንቁርናቸውን፣ ሆዳምነታቸውንና አድርባይነታቸውን  የሚገልፁ የቅሌት ስሞችን ማውጣት እና ማሰራጨት።

ማድነቅን - ለነፃነት ሲሉ ዋጋ የከፈሉ እና እየከፈሉ ያሉ ዜጎችን ማድነቅ፤ አርዓያነታቸውን ማጉላት፤ ማበረታታት፤ ሁለተናዊ ድጋፍ መስጠት።

ማብራራት - የሥርዓቱ አገልጋዮች አድርባይነት ከዚያም አልፎ ወንጀለኝነት በማስረጃዎች አስደግፎ ይፋ ማድረግ።   ስለ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፤ ሰለ ሀብት ዘረፋ፣ ስለ ሙስናን፣ ስለ መሬት ቅርምት፣ የባለስልጣኖች ሀብት ማሸሽን በሀገሪቱ ከተንሰራፋው እና እያደገ ከመጣው ድህነት ጋር እያነፃፀሩ ማቅረብ። አስከፊ ስለሆነው የእስረኞች አያያዝ በሀቅ ላይ የተመሠረቱ ጽሁፎችን በጋዜጦች፣ ሬድዮና ቴሌቪዥኖች መሰል መገናኛ ብዙሀን እንዲሰራጭ ማድረግ።
Dr. Tadesse Biru Kersmo