Monday 26 March 2018

ኢህአዴግ በጥርና የካቲት ያደረገው የፖለቲካ ውይይት


~ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ መፈታት አልነበረበትም

~የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን  የፓርላማ አባላት መቃወማቸው ጃዋር ፓርላማውን እንደተቆጣጠረው ያሳያል

~የኦሮሚያ የታችኛው መዋቅር ፈርሶ በቄሮ ተተክቷል፣

የፌደራል ጉዳዮች

የፖለቲካ ዘርፍ የጥር   እና የካቲት 2010  ሪፖርት

መጋቢት 2010

መግቢያ

የፌዴራል ጉዳዮች ኢህአዴግ ወረዳ በጥር እና በየካቲት 2010 ዓ.ም ከወቅታዊ ጉዳዮች እና ማረጋጋት ጋር የተያያዙ ስራዎችን ሰርቷል፣ በየብሄራዊ ድርጅቱም ተመሳሳይ ስራዎች እና አደረጃጀቶችን የማጠናከር ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ እነዚህም እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

~በወቅታዊ ጉዳዮች እና ማረጋጋት ላይ የተሰሩ ስራዎች

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ተካሄደ የመጀመሪያ ውይይት

የስብሰባው አጀንዳ፡-

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በታህሳስ 2010 ዓ.ም ያካሄደውን የ17 ቀናት ግምገማና ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች፣

የጓድ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ከስልጣን መልቀቅ ምክንያትና እንድምታው፣

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአሁኑ ጊዜ ድጋሚ መታወጁ አስፈላጊነት የሚሉ ናቸው፡፡

ውይይቱን የመሩ ጓዶች፡-

ጓድ ሙሉጌታ ውለታው፣ እና
ጓድ ካይዳኪ ገዛሃኝ፡፡
በስብሰባው የተገኙ አባላት ብዛት፡- 64
ስብሰባው የተካሄደበት ቀን፡- 20/06/2010

(ግማሽ ቀን)

አካሄድ፡- በጓድ ሙሉጌታ ውለታው በሶስቱም ርእሰ-ጉዳዮች ላይ በቂ ዝግጅት የተደረገበት ዝርዝር ማብራሪያ ለአባላት (Presentation) ከቀረበ በኋላ አባላት ሃሳባቸውን በግልፅነት እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡

በርእሰ-ጉዳዮቹ ላይ የቀረቡ አስተያየቶችና የተነሱ ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

የጓድ ሃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን መልቀቅን በተመለከተ፡-

የስልጣን መልቀቅያ አስገቡ ሲባል መጀመሪያ ሁሉም አባል እንደተደናገጠ፣ እና ወደ ጭንቅንቅና ስጋት እንደገባ፣ ህዝቡ ውስጥም መደነጋገር እንደተፈጠረ፣ አስደናቂ ክስተት እንደነበር!
ሆኖም የተፈጠረውን ሃገራዊ ችግር በመፍታት ሂደት ጓድ ሃይለማሪያም ራሱን የመፍትሄ አካል ለመሆን ብሎ የወሰደው እርምጃ መሆኑን፣ እስኪፈቀድለት ስራውን እየሰራ የሚቆይ መሆኑን ተደጋጋሚ በሚዲያ ሲገለፅ መረጋጋት እንደተፈጠረ፣  ጓዱ የመፍትሄ አካል ለመሆን ከስልጣን መልቀቁ ተገቢ ነው፣ በፈቃደኝነት ስልጣን መልቀቁ በአዎንታ የሚታይ ታሪካዊ ውሳኔ ነው፣ ለሌሎቹ አመራሮችም ትምህርት የሚሰጥ፣ ለሌሎች ሀገራትም ጥሩ ተሞክሮ (Exemplary) ነው፣ በመልቀቁ አብዛኛው ጥሩ አስተያየት አለው፣
ነገር ግን እንዲለቅ ምክንያት የሆኑት ዝርዝር

ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

ሁለት ተቃራኒ አስተያየቶችም ተንፀባርቀዋል፡-
በአንድ በኩል የጓድ ሃይለማሪያም ብቃት ጥሩ ነው፣ ብዙ ስኬቶችን ልንጠቅስለት እንችላለን፣ ሆኖም ድክመቱ እርምጃ መውሰድ ላይ እንደሆነ፣ የዘገየ Resignation መሆኑ፣ በክብር መሸኘት እንደሚገባው፣

በሌላ በኩል ደግሞ የጓድ ሃይለማሪያም ከስልጣን መልቀቅ ጊዜው አይደለም፣ እንዲሁም የጓድ በረከትና የጓድ አባዱላ መልቀቅያ ተቀባይነት ያለማግኘቱና የጓድ ሃይለማሪያም መልቀቅያ ተቀባይነት ማግኘቱ Double Standard ነው፣ ሌላ ትርጉም ይኖረዋል፣

ጓድ ሃይለማሪያም ደካማ መሆኑ በኢህአዴግና በደኢህዴን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ተገምግሟል፣ በፈቃደኝነት ለቀቀ የተባለው ሽፋን ነው፣
በ17 ቀናት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የግምገማ መድረክ ላይ ለምን Resign አላደረገም? መጀመሪያ ተግባብተው ነበር ወይ? (ጥርጣሬ ይፈጥራል)፣

ለምን ሃይለማሪያም ብቻ ይለቃል? ካቢኔውስ ለምን አይጠየቅም? ምን ስር-ነቀል ለውጥ ይመጣል? የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የጓድ ሃይለማሪያምን የስልጣን መልቀቅያ ጥያቄ የተቀበለው በቀናነት (Genuinely) ነው ወይ? የ4ቱ ብሄራዊ ድርጅቶች አመራሮች አምነውበታል?

የኢህአዴግ ም/ቤት የስልጣን መልቀቅ ጥያቄው ባይቀበለውስ?

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድጋሚ መታወጁ ያለው አስፈላጊነትን በተመለከተ፡-

በአሁኑ ጊዜ የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ትክክል መሆኑ፣ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፣ ሻዕብያ ኢትዮጵያን ለመበታተን እየተረባረበ ነው፣ ኢህአዴግ ከመበታተን አድኖናል፣
ነገር ግን አዋጁ በትክክል ይተገበራል ወይ? ደንቢ ደሎ፣ ነቀምት፣ ጎንደር እየተጣሰ አይደለም ወይ? የህግ የበላይነት እየተሸረሸረ ነው፣
የመጀመሪያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት አልነበረበትም፣ አሁንም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጎን ለጎን መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ስራዎች መሰራት አለባቸው፣
ሆኖም በአዋጁ ላይ ለህዝቡን ማስረዳት አለብን፣ ስለ አዋጁ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ለጋዜጠኞች በቂ ዕድል አልተሰጠም፣ጥቂት ጥያቄዎች ብቻ ናቸው የተስተናገዱት፣
አዋጁ በፓርላማ እንዳይፀድቅ የሚደረግ ጥረት መኖሩን፣ የፓርላማ አባላት አዋጁን እንዳያፀድቁት ጫና መፍጠርና ማስፈራራት እንዳለ፣ የፓርላማ አመራሮች መስራት እንዳለባቸው፣ በዚህ ዙሪያ ላይ ካድሬው የራሱን ላፊነት እየተወጣ እንዳልሆነ፣
መከላከያ ከክልላችን ይውጣ የሚለው ህዝቡ ላይ ሆን አመራሩ እንደሆነ፣

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ግምገማና አቅጣጫዎችን በተመለከተ፡-

ኢህአዴግ እንዴት እየገመገመ ነው? የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ታህሳስ ወር ያካሄደውን ግምገማ እንደጨረሰ በወቅቱ ማብራሪያ ተሰጥቶ ነበር፣ ሆኖም ችግሩን በትክክል ለይተው ፈትተውት ነበር ወይ?
በየብሄራዊ ድርጅቱ የተካሄዱ ግምገማዎች የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባስቀመጠው አቅጣጫ እየሄዱ ነበር ወይ? በአሁን ዚዜ ከተለመደው የኢህአዴግ ባህሪ ውጭ የስልጣን ቅስቀሳ እየተካሄደ ነው፣ አመራሮቻችን አንድ ላይ ሆነው እየመሩን ነው ወይ?
ችግር ለድርጅታችን አዲስ አይደለም፣ አሁን ግን አመራሩ ፅናት ይጎድለዋል፣ ችግር የመፍታት ብቃት ያንሰዋል፣ ድርጅቱ አባላትን እያገኘ እየመራ አይደለም፣ የመረጃ ምንጫችን Facebook ነው፣ ፊት ሆነን ቀድመን እየመራን ስላልሆነ ሁኔታው ቀድሞን ሊያጠፋን ይችላል፣
የአባዱላ ከአፈ-ጉባኤነት መውጣትና መመለስ ለአባላት ግልፅ አይደለም፣
ለህዝቡ የሚሰጡት መግለጫዎች ህዝቡን እያደነባበሩት ናቸው፡፡
ኢህአዴግ ደካማ ድርጅት ነው ቢባልም እንኳ ጠቃሚ ድርጅት ነው፣
የኦሮሚያ የታችኛው መዋቅር ፈርሶ በቄሮ ተተክቷል፣
የብሄራዊ ድርጅት ዋሻ ካልፈረሰ መፍትሄ አይመጣም፣ ሕብረ-ብሄራዊ ፈዴራል ስርዓቱ አሳታፊ በሆነ መልኩ ይፈተሸ፣
የኦሮሚያ የቋንቋ ጥያቄም ተወያይቶ መልስ ለምን አይሰጥበትም? ቢፈቀድስ ምን ችግር አለው?
እስረኞች አፈታት ላይ ችግር አለ፣ ሰውን የገደሉ ወንጀለኞች ተለቀዋል፣ ከመስፈርቱ ውጭ ተፈፅሟል (ምሳሌ ኮሎኔል ደመቀ)፣
መሆን አለበት ተብሎ የተጠቆሙ ጉዳዮች፡-
ከምንም ጊዜ በላይ ልንረባረብ ይገባል፣ አመራሮቻችን አንድ ላይ ሆናችሁ ምሩን፣
መንግስት ከማንም ጊዜ በላይ ጠንካራ መሆን አለበት፣
የድርጅት መዋቅሩ/አባሉ ቀድሞ መወያየት አለበት፣ ከእኛ ምን ይጠበቃል በሚለው ላይ አተኩረን ተደራጅተን መታገል፣ መቀናጀትና በፅናት መጋፈጥ፣ እና Proactively መስራት ያስፈልገናል፣

የሚዲያ መግለጫዎች ጥንቃቄ ይደረግባቸው፣ የስልጣን ሽሚያ የሚመስሉ ገለፃዎች እየተላለፉ ናቸው፣
ማጠቃለያ፡-
ከፍ ብሎ በተዘረዘሩት አስተያየቶችና ጥያቄዎች ላይ በአባላትና በመድረኩ መሪዎች ላይ ሰፊ ማብራርያ ከተሰጠ በኋላ ልዩነት ሳይኖር የጋራ መግባባት በመፍጠር ተጠቃልሏል፡፡  
በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ ውይይት
የስብሰባው አጀንዳ፡- ወቅታዊ ሁኔታ ያለበት ደረጃና የአባላት ስምሪት፣
ውይይቱን የመሩ ጓዶች፡-
ጓድ ነጋ አደሬ፣ እና
ጓድ ፀጋብርሃን ታደሰ፡፡
በስብሰባው የተገኙ አባላት ብዛት፡- ወንድ 75፣ ሴት 13፣ ድምር 88፡፡ በተለያየ ስራ ምክንያት በስብሰባው ያልተገኙ አባላት ብዛት 50 ናቸው፡፡
ስብሰባው የተካሄደበት ቀን፡- 28/06/2010 (ግማሽ ቀን)
አካሄድ፡- በፌዴራል ዞን አመራር በ26/06/2010 ዓ.ም በወቅታዊ ሁነታና የአባላትን ስምሪት አስመልክቶ የተሰጠውን ማብራሪያና ኦሬንቴሽን መሰረት በማድረግ በጓድ ነጋ አደሬ ዝርዝር ማብራሪያ ለአባላት ቀርቧል፡፡ በማብራርያው ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች፣
(ሀ) ወቅታዊ ሁኔታ ያለበት ደረጃ
በአሁኑ ጊዜ በሃገራችን እየተካሄደ ያለው ዓመፅ የቀለም አብዮት መሆኑን፣ የሃገራችን ፀጥታ ሁኔታ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን፣
የጠላት ግምገማ መላ ሃገሪቱ በቁጥጥሩ ስር ማድረጉንና አዲስ አበባን በመክበብ፣ ማንኛውም ነገር እንዳይገባ በመዝጋት ህዝቡ እንዲቸገርና ከውስጥ ዓመፅ እንዲነሳ በማድረግ ለመጨረሻ ጊዜ መንግስት ማፍረስ ይቻላል የሚል መሆኑን፣
ሆኖም እተካሄደ ያለው ዓመፅ በተደራጀና በሰለጠነ ሃይል የሚመራ ሳይሆን ከውጭ በሚሰጥ ትእዛዝ የሚፈፀም መሆኑን፣
የቀለም አብዮቱን እየመሩና እያቀጣጠሉ ያሉት ሃይሎች አክራሪው ኒዮ ሊበራል ሃይል፣ ሻዕብያ፣ ግብፅ፣ ፅንፈኛው ዳያስፖራ መሆናቸው፣
በአገር ውስጥ በኦሮሚያ ጥቂት ወጣቶች ለገንዘብ ብለው በእነዚህ ሃይሎች በሚሰጥ ትእዛዝ አማካኝነት የቀለም አብዮቱ አቀጣጣዮች ሆነው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው፣ ሆኖም አብዛኛው ወጣት በእነዚህ ወጣቶች ስር የተደራጀ ሳይሆን ዓመፅ በሚቀሰቀስበት ጊዜ በስሜታዊነት የሚከተላቸው መሆኑን፣ ህዝቡ ግን ሰላም የሚፈልግ መሆኑን፣
ሃገሪቱ ከገባችበት የፀጥታ አደጋ ለመታደግ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ትግል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን፣ አዋጁ መላ ሃገሪቱን የሚሸፍን ሆኖ ነገር ግን በሁሉም አካባቢዎች እኩል ክብደት እንደማይኖረው፣
ጠላት የቀለም አብዮቱን ለማሳካት የርብርብ ማዕከል ያደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ እንዳይሆን ማድረግ እንደሆነ፣ በዚህ ምክንያትም በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል በሁሉም አካባቢዎች የንግድና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መዘጋቱን፣ አዲስ አበባም ከአራቱ አቅጣጫዎች የግብርናም ይሁን የፋብሪካ ምርት እንዳይገባ በመዝጋት የፍጆታ ዕቃዎች እጥረት እንዲከሰትና ከዚህ በመነሳት ከውስጥ ዓመፅ እንዲነሳ ርብርብ እየተደረገ ነው፣ 
(ለ) በአሁኑ ጊዜ የሚኖረን ተልዕኮ
በአሁኑ ሰዓት ሃገሪቱ በቀለም አብዮት አማካኝነት ካጋጠማት አደጋ ለማውጣት በየተቋሞቻችንና በመኖሪያ አካባቢ ከአበባ በአዲስ ጋር በመቀናጀት የሚሰሩ ስራዎች አሉ፡፡ ማዕከል የምናደርገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መተግበር ሲሆን ትኩረታችንም ፀጥታን ማስከበር/ማስጠበቅ ነው፡፡ በዚህ መሰረት
በየተቋሙ የሚሰሩ
አባሉና ሲቪል ሰራተኛ በየተቋሙ መደበኛ የመንግስትን ስራ በጥብቅ እንዲፈፅም፣ አገልግሎት ምንም ምክንያት እንዳይቋረጥ ማድረግ፣ ፌስ ቡክና ሌሎችን አሉቧልታዎች እያዳመጠ ከስራ ውጭ እንዳይሆን ማድረግ፣ ጥብቅ ቁጥጥር መካሄድ ይገባል፣
አንዳንድ ሰራተኞች የቀለም አብዮቱን አራማጆችና መልእክተኞች ሊሆኑ ስለሚችሉ ሆን ብለው Sabotage ሊፈፅሙ ይችላሉ፣ ይህንን በጥብቅ መከታተልና ተፈፅሞ ሲገኝም መቆጣጠር ይገባል፣
ከዚህ በፊት የነበሩ አደረጃጀቶች (የስራ ሂደት ፎረም፣ የለውጥ ቡድን/1-ለ5 አደረጃጀት፣ የስራ ሂደት ፎረምና ሌሎችም አደረጃጀቶች) የበለጠ ውይይትና መግባባት የሚፈጠርባቸው በማድረግ ለሰላምና ለሕገ-መንግስት እንዲቆሙ ማድረግ ይገባል፣
በየተቋሙ በወቅታዊ ሁኔታ ላይ የጠቅላላ ሰራተኞች መድረክ በመፍጠር ማወያየትና በቂ ግንዛቤ ይዘው ለሰላም እንዲቆሙና መደበኛ ስራቸውን በጥብቅ እንዲያከናውኑ ማድረግ እንደሚገባ፣ አባላት ግንባር ቀደም ሆኖው መስራት እንደሚገባቸው የሚሉ በዝርዝር ቀርበው መግባባት ተደርሶባቸዋል፡፡ 
በመኖሪያ ሰፈር የሚሰሩ ስራዎች
በአዲስ አበባ ደረጃ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅም ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን፣
ሁሉም አባል ከዛሬ ጀምሮ ወደ መኖሪያ ሰፈር ወረዳ በመሄድ ሪፖርት ማድረግ እንደሚገባ፣ ከወረዳው በሚሰጥ ተልዕኮ መሰረት አብሮ መስራት እንደሚገባ፣ አዋጁን ለመጣስ የሚሞከሩ ሙከራዎችን በመከታተል ማክሸፍና ሪፖርት ማድረግ እንደሚገባ፣
ከኦሮሚያ ጋር የሚዋሰኑ የአዲስ አበባ ወረዳዎች የሚኖሩ አባሎቻችን ደግሞ ከኦሮሚያ ጋር ቅንጅት በመፍጠር በጋራ መስራትና የመረጃ ልውውጥ ማድረግ እንዳለባቸው፣ የሚሉትን በማቅረብ ውይይት ተካሂዶ መግባባት ተፈጥሯል፡፡
(ሐ) በውይይቱ ከአባላት የተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች
ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ተደጋግሞ ስብሰባ መጠራቱ ጥሩ ነው፣ አሁን ችግሩ ሁላችንም ያጠፋናል፣ ስለሆነም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈፀም እንሰራልን፣
አሁን ህዝቡ የመብራትና ውሃ ጥያቄ እያነሳ አይደለም፣ በሂወት የመቆየት የሰላም ጥያቄ ነው እያነሳ ያለው፣
ነገር ግን የተገመገመ ተጨባጭ ውጤት ጠብቀን ነብር፡፡ ኢህአዴግን ወክሎ ፓርላማ ውስጥ ያለው አባል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መቃወሙ በጁሃር ጎራ የተሰለፈ መሆኑን ያረጋግጣል፣ ይህ ጉዳይ ተገምግሞ ከኢህአዴግ የወጣ ጎራ ነው መባል ነበረበት፡፡ ስንታገል ማን ከማን ጋር ተሰለፈ በማለት በግልፅ ለይተን መሆን አለበት፡፡ ከኢህአዴግ አቋም መውጣት ማዕከላዊነትን መጣስ ነው፣ ማዕከላዊነትን መጣስ አያስጠይቅም ወይ? በዚህ ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አስፈላጊነትን በተመለከተ በዝርዝር ተወያይተን ስምምነት ላይ ደርሰን ነበር፣ አዋጁ ወደ ምክር ቤት ሲቀርብ የኦህዴድ አባላት መቃወማቸው ሰላምን አይፈልጉም ወይ? በፓርላማው ውስጥ የተፈጠረ ልዩነት የኦህዴድ አቋም ነው ወይ (በግልፅ ይቅረብልን)?
በኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ሁከት አስመልክቶ የኦህዴድ አመራር መግለጫና ማብራሪያ ለምን አይሰጥም? ለምን ሁሉም ነገር ለፀጥታው ሃይልና ኮማንድ ፖስት ይተዋል? የኦህዴድ ካድሬ ለምን ሱቆች እንዲከፈቱ አያደርግም? ካድሬው አሰላለፉ ከማን ጋር ነው፣ የት ነው ያለው? ለምን ኦሮሚያ ውስጥ የመንግስት መስሪያ ቤት ይዘጋል? ለምን አይጠየቅም? ይህ ኦሬንቴሽን ለኦሮሚያ ካድሬዎችም እየተሰጠ ነው ወይ? የኦህዴድ አባላት ምን እየሰሩ ናቸው? ከማን ጋር ሆነን ነው የምንታገለው? 
የቀለም አብዮት እየተካሄደ ነው ብለን ከዚህ በፊት ደጋግመን ገልፀን ተቀባይነት አላገኘም ነበር፣ አሁን ተቀባይነት ማግኘቱ ጥሩ ነው፣ ግን አሁን የቀለም አብዮት አራማጅ ራሱ የኢህአዴግ አባል ነው፣ ችግርን መፍታት አቅቶናል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ስለምንኖር አሁን በአዲስ አበባ መስተዳድር ውስጥ ያለው አባል የፖለቲካ ቁመናው ወርዷል፣ ጎጠኝነትና ጠባብነት የተስፋፋበት ነው፣ የፌስ ቡክ ወሬ አቀባባይ በአጠቃላ አባላችን ነው፣
የመንግስት ሚዲያ የቀለም አብዮትን ማጋለጥ ሲገባው አሁንም የመልካም አስተዳደር ችግር እያለ ያወራል፣ ሰላም በሌለበት የመልካም አስተዳደር ችግር ለፈታ አይችልም፣ ህዝቡም ጥያቄው የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈታለ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ህዝቡ ሳይፈልግ ስራ እንዲያቆም እየተገደደ ነው፣ ሱቅ ለመክፈትና ስራውን ለመስራት ዋስትና አጥቷል፡፡
የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ እየተቀዛቀዘ ነው፣ ስብሰባ ነው፣ ወዘተ እየተባለ ቁጥጥርም እየላላ ነው፡፡ ችግር እየፈጠረ ያለው አመራር ነው፣ ወንጀለኞችን እየለየ መያዝና መጠየቅ አይፈልግም፣ ሰራተኛ እንዲቀዛቀዝ የሚያደርገውም ይህ ነው፣
መንገድና ንግድ እየተዘጋ እስከ መቼ ልንቀጥል ነው? ኢትዮጵያ እንደ ቴሌቭዥን የምትዘጋና የምትከፈት ሃገር መሆን የለባትም፣
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ በታህሳስ 2010 ዓ.ም ለ17 ቀናት ባካሄደው ግምገማ መተማመን ተፈጥሮ ነበር ወይ? ከሰማይ በታች ያለውን ሁሉ አንስተን ተወያይተናል፣ ተግባብተናል ብለው መግለጫ ከሰጡ በኋላ ለምን እንደገና ችግር ተፈጠረ? ለምን በመርህ መመራት አቃተን? ወዘተ… የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው በቂ ማብራርያ ከተሰጠ በኋላ የጋራ አቋም በመያዝ በየክፍለ ከተመማና ወረዳ በመሄድ ለመስራትም ስምምነት ተፈጥሯል፡፡

ሌሎች ስራዎች

ከፍ ብሎ ከተገለፀው በተጨማሪ ባለፌት ሁለት ወራት የሚከተሉት ስራዎችም ተሰርተዋል፡፡
የአዲስ ራእይ የመጨረሻው እትም በቁጥር 100 በመግዛት ለአባላት ተሰራጭቷል፣
በአዲስ ራዕይ መፅሄት የወጣው ‘ኒዮ-ሊበራሊዝም ሸሸ ወይስ አፈገፈገ’ የሚለው ርእሰ ጉዳይ አጠር ብሎ ተዘጋጅቶ በወረዳ ደረጃ ውይይት ተካሂዶበታል፣ ቀጥሎም በህዋስ ደረጃ ውይይት ተካሂዶበታል፣
በየተቋሙ የመንግስት ሰራተኞችን በመሰብሰብ በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

Tuesday 13 March 2018

የአግ7 አርበኞች ነዳጅ በጫነ የህወሓት መከላከያ ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት ፈፀሙ

መጋቢት 03 ቀን 2010 ዓ/ም ከሱዳን ካርቱም ለህወሓት ገዳይ አጋዚ ጦር አገልግሎት የሚውል ነዳጅ የጫነ ተሽከርካሪ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ደበጫ እንዳለፈ አማኑኤል ከተማ መግቢያ ላይ የአግ7 አርበኞች በደፈጣ በወሰድት እርምጃ ነዳጅ የጫነው ቦቴ ከነ ተሳቢው ሙሉ በሙሉ ጋይታል ፡፡ ይህ ከባድ ቦቴ መኪና ከነ ተሳቢው በጠቅላላ 44,000(አርባ አራት ሽህ ) ሌትር ቤንዝል ጭኖ የነበረ ሲሆን ተሽከርካሪውም ከነ ነዳጅ ሙሉ በሙሉ ተቃጥላል ፡፡ ህወሓት በአሁኑ ሳዓት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ኑፁሀንን በጠራራ ፀሀይ በግፍ እየጨፈጨፈ በሚገኝበት ወቅት ለዚህ እኩይ ስራው ዋና ጉልበቱ ነዳጅ በመሆኑ በዚህ ላይ በተጠና መንገድ ዘመቻው የተከናወነ መሆኑን የአግ7 መረጃ ክፍል ገልፃል ፡፡ በመሆኑም ይህ እና ሊሎች መሰል እርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ እየገለፅን ማንኛውም ለዚህ ዘረኛ ስርዓት አገልገሎት በሚውሉ ንብረቶች ላይ በተጠናከረ ፣ንገድ እርምጃው ይቀጥላል ፡፡ በዚህ ዘመቻ የተሳተፋ የአግ7 አርበኞች በሰላም ወደ ቦታቸው ተመልሰዋል ፡፡ ድል ለሕዝብ !!! የአግ7 ዘመቻ ነፃ ትውልድ ፡፡ 

Sunday 15 October 2017

ለኢትዮጵያ የመከላከያና ፓሊስ ሠራዊት አባላት የተደረገ ጥሪ

ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር
በድጋሚ የቀረበ

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፤ የፌደራልና የክልል ፓሊስ አባላት፤ የአጋዚ ልዩ ኮማንዶ ጦር አባላትና ሌሎች የሥርዓቱ ታጣቂዎች። አገራችን በለውጥ ሂደት ውስጥ ባለችበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ለእናንተ ቀጥታ መልዕክት ማስተላለፍ የሚገባ ሆኖ ስላገኘሁት ይህንን አጭር መልዕክቴን በጥሞና እንድታዳምጡኝ፤ የሰማችሁ ላልሰሙት እንድታደርሱልኝ እጠይቃለሁ።

የአገር መከላከያ ሠራዊት አባል መሆን ከፍተኛ ክብር ያለው ሙያ እንደነበር የምታውቁት ነው። ለሀገር ዘብ መቆም መልካም ዜጎች ሁሉ የሚመኙት ተግባር ነው። አንድ ሰው ቃለ መሀላ ፈጽሞ የመከላከያ ሠራዊት ዩኒፎርም ከለበሰ በኋላ ተራ ዜጋ አይደለም። አገሪቷ በዜጎቿ ማየት የምትፈልጋቸውን መልካም እሴቶችን ሁሉ በወታደሮቿ ማየት ትሻለች፤ ለሕዝብ ተቆርቋሪነት፣ ሀገር ወዳድነት፣ ፍትሀዊነት፣ ጀግንነት፣ ታማኝነት በወታደሮቿ ማየት ትሻለች። ለዚህም ነው በብዙ አገሮች ውስጥ ያሉ ሕፃናት “ስታድጉ ምን መሆን ትፈልጋላችሁ?” ሲባሉ ከሚሰጧቸው መልሶች ግንባር ቀደሙ “ወታደር” የሚሆነው። በሀገራችንም ዘመናዊ ጦር ከመደራጀቱ በፊት አያት ቅድም አያቶቻችን ራሳቸውን በወታደርነት አሰልጥነው፤ ወራሪ ሲመጣ በየጎበዝ አለቆቻቸው እየተቧደኑ ዘመናዊ ጦሮችን ሳይቀር ተዋግተው በማሸነፍ የአገራችንን ሉዓላዊነት አቆይተውልናል። ዘመናዊ ጦር ከተደራጀ ወዲህም እስከ ህወሓት አገዛዝ የነበሩ አስተዳደሮች ብዙ እንከኖች ቢኖርባቸውም እንኳን የመከላከያ ሠራዊትን የአገር መከላከያ ሠራዊት አድርገውት ቆይተዋል። የሠራዊቱን ክብርና ሞገስ ለመጠበቅም የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። ይህ ጥረት ግን በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ሙሉ በሙሉ ተቀልብሷል።

የፓሊስ ሠራዊት ሥራ ለሕዝብ የዕለት ተዕለት ኑሮ ዋስትና መስጠት ነው። ዜጎች በሰላም ከቤታቸው ወጥተው በሰላም የመመለሳቸው ዋስትና ከወገናቸው ከፓሊስ ሊያገኙ ይሻሉ። ሕዝባዊ ፓሊስ የወሮበሎች፣ የሌቦችና የማጅራት መቺዎች ጠር፤ የድሆችና ደካሞች አጋር ነው። ሕዝባዊ ፓሊስ የፍትህ ጠበቃ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ፓሊስ በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ማየት አልቻልንም።

የህወሓት አገዛዝ የተከበሩትን የውትድርናና የፓሊስ ሙያዎችን አዋርዶ ለሀገርና ሕዝብ ደህንነት ሳይሆን ለአንድ ቡድን ሥልጣን መከበር የቆሙ ኃይሎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። አሁን ያለው የኢትዮጵያ መከላከያና የፓሊስ ሠራዊትን ስናስብ በአዕምሮዓችን የሚመጡት የሚከተሉት ሀቆች ናቸው።

የጦር ሠራዊቱ፣ ብቃትና ዕውቀት እንዲሁም የሀገር ፍቅር ባላቸው ጄኔራሎችና የጦር መኮንኖች የሚመራ ሳይሆን በተቃራኒው ምንም ዓይነት ወታደራዊ ትምህርት በሌላቸው ከሽምቅ ውጊያ ቡድን አዛዥነት ወደ ዘመናዊና መደበኛ ጦር አዛዥነት በድንገት ያደጉ፤ ራሳቸውን ከዘመናዊ ሠራዊት አደረጃጀትና አመራር ጋር ያላዋሃዱ፤ ከሀገር ጥቅም ይልቅ የራሳቸው የግል ጥቅም የሚበልጥባቸው፤ የማይጠረቁ ስግብግቦች፤ ታማኝነታቸው ለሀገር ሳይሆን አባል ለሆኑባቸው ፓርቲዎች የሆኑ ግለሰቦች ናቸው።

ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ ሠራዊት በወያኔየስለላ መረብ ተተብትቦ ወይም በእነርሱ ቋንቋ “ተጠርንፎ” በግድ የተያዘ እንደቁም እስረኛ ሊቆጠር የሚችል በከፍተኛ ምሬትና በደል ውስጥ የሚገኝ ሠራዊት መሆኑን እናውቃለን። የሠራዊቱን ክብር በሚነካ፤ ስብዕናን በሚያዋርዱ ዘለፋዎችና በግምገማናላው እንዲዞር፣ ሞራሉ እንዲላሽቅ የተደረገ ሠራዊት ነው። የህወሓት ጄኔራሎችና ካድሬዎች የሚያወርዱበት ዘለፋና ስድብ የዕለትተዕለት ቀለቡ የሆነ፤ ሞራሉም የላሸቀ ሠራዊት ነው።

አንድ ተራ የህወሓት ካድሬ ወይንም የበታች ሹም የዘረኛው ሥርዓት በሚሰጠው ልዩ ግምትና ስልጣን ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች የመጡ በማዕረግም በዕውቀትም የበላይ የሆኑንትን ሻለቆችና ኮሎኔሎችን የሚያንጓጥጡበት፣ የሚያዋርዱበትና የሚያሸማቅቁበት፤ አመራሩበወታደራዊእዝና ወታደራዊ ስነምግባር መሠረት የሚመራሳይሆንበብሄር የበላይነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ዲሲፕሊንና ውህደት የሌለው ሠራዊት ነው። በብሔር የተከፋፈለ በመሆኑ በውስጡ ያለው ጓዳዊ ስሜት በእጅጉ የላላ ሠራዊት ነው።

የፍትህ ጥያቄየሚያነሱ የሠራዊቱ አባላት ለህወሓት ካድሬዎች ስላልጣማቸው ብቻ ያለ ወታደራዊ ህግና አግባብበ አንድ የህወሓት ካድሬ ትዕዛዝ ብቻ ደብዛቸው ሊጠፋ እንደሚችል ስለሚያውቁበከፍተኛ የፍርሃት እና በራሳቸው ላይ እምነት እንዲያጡ የተደረጉ ናቸው።
ይህ ሠራዊት ለወያኔ ጠባብ አጀንዳ በየግንባሩ ዘመቻ እንዲሄድ ሲገደድና ሲማገድ የህወሓት ካድሬዎችና ጄኔራሎች የሕይወትና የደም ግብር እንዳይከፍሉ ከአደጋ እንዲጠበቁ የሚደረግበት ዘዴና ስልት የተቀየሰበት የዘረኝነትና የአድሎ ሥርዓት ውስጥ የተጣደ ሠራዊት ነው።
ሠራዊቱ ሲቆስል፣ ደሙን ሲያፈስ፣ ፈንጂ ሲረግጥ፣ ሕይወቱን ሲገብር የህወሃትቅምጥል ጄኔራሎችና መኮንኖች ቅጥባጣ አስረሽ ምችው በየከተማው እንደሚባልጉ የሚያውቅ ሠራዊት ነው።

ጫማና የደንብ ልብስ ከዚያም አልፎ የሚበላዉን ምግብ ከሚከፈለዉ ትንሽዋ ደሞዙ ላይ እየተቆረጠበት እናት አባቱን ለመጦር እና ልጆችን ለማሳደግፈተና ውስጥ የሚገባ፤ ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተዳረገ ሠራዊት ሆኖ ሳለ በአንፃሩ የህወሓት ጄኔራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች በኮንትሮ ባንድ ንግድና በዘረፋ ሲከብሩ፤ ንግዳቸውን በግላጭ ሲያጧጥፉ፤ ባለብዙ ህንፃዎች ባለቤቶች በመሆን በዘመድ አዝማዶቻቸዉ ስም ጭምርሀብት ሲያካብቱ፤ የህዝቡን መሬት ያላግባብ ሲቀሙና ሲቀራመቱ፤ በሰላም አስከባሪ ኃይል ስም በተባበሩት መንግስታት በየሀገሩ እየተመደቡ በወር እስከ 25,000 የአሜሪካ ዶላር ተከፋይ ሆነው ሲቀማጠሉ በሚገባ እያስተዋለ የሚገኝ ሠራዊት ነው።

በተጨማሪም እንደው ድንገት ለምርጦቹ የሚደርሰው የሰላም ማስከበር ተሳትፎ ግዳጅ ሲሄድ ሊያግኝ ከሚገባው የኪስ ገንዘብ ላይ አብዛኛውን ለራሳቸዉ ጥቅም በማዋል እና ሀገሪቷ ከዚህ ከሰላም ማስከበር ልታገኝ የሚገባትን ጥቅማጥቅም በራሳቸዉ በህዉሃት ጄኔራሎችና አመራሮች የግል ኪስ በማስገባት ራሳቸውንና ዘመድ አዝማዶቻቸዉን እያበለጸጉበት ይገኛሉ።

ሠራዊቱ ከትንሿ ደመወዙ ለመለስፋዉንዴሽን፣ ለአባይግድብግንባታ፣ ለተለያዩ የተሃድሶ መዋጭዎች፣ ለአመት በአል ድግሶች መዋጮ እንዲፈል የሚገደድ ምስኪን ነው። አላዋጣም፤ ገንዘብ የለኝም ብሎ ቢል ጸረ ሰላም ወይንም ሌላ ስም ተሰጥቶት ለተለያዩ አይነት ቅጣቶች ይዳረጋል። ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ቢከለክልም እንኳን በሰራዊቱ ውስጥ የድብቅ የሕወሀት አደረጃጀት ፈጥሮ በሰራዊቱ ውስጥ የልጅና የእንጀራ ልጅ ስሜት ፈጥሮ የሚከፋፍል እኩይ ኃይል ነው ይህን ሰራዊት የተቆጣጠረው።

በፌዴራል ፖሊስና በአጋዚ ልዩ ኮማንዶ ውስጥ ነግሶ የሚታየው ሁኔታ ከላይ ከዘረዘርናቸው የተለየ አይደለም። ሠራዊቱ የአዛዦቹ አገልጋይ በመሆን የበይ ተመልካች የሆነበት መዋቅር ነው። ሞት፣ የአካል መጉደልና ድህነት ለሠራዊቱ አባላት፤ በአንፃሩ ምቾችና ድሎት ግን ለአዛዦቹ እንዲሆን ታቅዶ የተደራጀ ሠራዊት ነው።

ኢትዮጵያ በየዘመኑ እያደገና እየዘመነ የመጣ ሞያን፣ ችሎታንና ወታደራዊ ሳይንስን አዳብሎ የታጠቀና ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተዉጣጣ ዘመናዊ የአገር መከላከያ ተቋም የነበራት አገር ነበረች። ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ ይህንን ዘመናዊ የአገርና የወገን መከታ የሆነዉን ሠራዊት አፍርሰዉና ለእናት አገሩ የተዋደቀዉን ሠራዊት ለማኝ አድርገዉት ነዉ በህወሓት የበላይነት የሚመራ አዲስ የመከላከያ ሠራዊት የገነቡት። ይህ ህወሓት የገነባዉ ሠራዊት በአደረጃጀቱም ሆነ በቀን ከቀን ስራዉ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ጋር በምንም መልኩ የተገናኘ አይደለም። ይህንን መከላከያ ሠራዊት የፈጠረዉ ህወሓት፣ የሚመራዉና የሚቆጣጠረዉ ህወሓት፤ ሠራዊቱ በሚወስዳቸዉ እርምጃዎች ሁሉ ዋነኛዉ ተጠቃሚም የህወሓት/ኢህአዴግ ጥቂትዘራፊ መሪዎች ብቻ ነዉ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሆይ!

ህወሓት/ኢህአዴግ ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ የደገሰዉ የጥፋት ተልዕኮ ካልተሳካ አንተን እንደለመደዉ ሜዳ ላይ በትኖና ባንተ ትከሻ ላይ እንደመዥገር ተጣብቆ የዘረፈዉን የአገር ሀብትና ንብረት ይዞ አገር ለቅቆ እንደሚጠፋ ምንም ጥርጥር የለዉም። ለዚህ የሽሽት ጉዞዉ ደግሞ ለረጂም ግዜ ተዘጋጅቷል። በቢልዮኖ ዶላሮች የሚቆጠር ሀብት በውጭ ሀገሮች አስቀምጧል። በዚህሠራዊት ዉስጥ የአገሩን ዳር ድንበር የጠበቀ እየመሰለዉ የህወሓት መሳሪያ ሆኖ የራሱን ወገኖች ከሚገድለዉ ኢትዮጵያዊ ዉስጥ ከአስር ዘጠኙ የህወሓት/ኢህአዴግን መወገድ የሚናፍቅ ዜጋ ነዉ። ችግሩ ይህ ሠራዊት ልክ እንደ ሲቪል ወግኖቹ በዘርና በቋንቋ ተለያይቶ የተደራጀ በመሆኑ እርስ በርስ ተገናኝቶ መነጋገርና መወያየት አለመቻሉ ነው።

ይህ ሙሉ በሙሉ በህወሓት ቁጥጥር ስር የሚገኘዉ ሠራዊት ባለፉት ሀያ አምስት ዓመታት የወሰዳቸዉን ፀረ ሕዝብና ፀረ አገር እርምጃዎች አንድ በአንድ ስንመለከት ይህ ተቋም በሚወስዳቸዉ እርምጃዎች የሚጎዳዉ የሠራዊቱ ጡንቻ የሚያርፍበትን የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የሠራዊቱ አባላት እራሳቸዉም የራሳቸዉ እርምጃ ሰለባዎች ናቸዉ። ታድያ ለምንድነዉ ይህ ሠራዊት ከ25 አመት በላይ እሱን እራሱን፣ እናቱን፣ አባቱን፣ እህቱንና ወንድሙን የሚጎዳ እርምጃ የሚወስደዉ? የአገርን ዳር ድንበር ከባዕዳን ወራሪዎች ለመከላከል የተደራጀና የታጠቀ መከላከያ ሠራዊት ለአዛዦቹ መታዘዝ እንዳለበት ከማንም የተሰወረ አይደለም። ሆኖም አንድ የአገሬን አንድነትና የወገኖቼን ደህንነት እጠብቃለሁ ብሎ ቃለ መሃላ የፈጸመ የመከላከያ ሠራዊት አባል ደህንነቱን መጠበቅ የሚገባዉን ሕዝብ በነጋና በጠባ ግደል ተብሎ ትዕዛዝ ሲሰጠዉ ትዕዛዙን ከመፈጸሙ በፊት ማንን ነዉ የምገድለዉ ለምንስ ነዉ የምገድለዉ ብሎ እራሱን መጠየቅ አለበት።

ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘመናዊ የባርነት አዋጅ ታዉጆበታል። ህወሓት ይህንን አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ የሚሯሯጠዉ አንተን ከሕዝብ አብራክ የወጣኸዉን የሕዝብ ልጅ በመጠቀም ነዉ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ ሀይል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነትና እኩልነት ይዋጋል እንጂ እሱንና ወገኖቹን የህወሓት ባሪያ የሚያደርግን አዋጅ አያስፈጽምም። ይህ አገርንና ሕዝብን ለመጠበቅ ህገ መንግስታዊ አደራ የተሸከመ ሠራዊት የታጠቀዉን መሳሪያ ማዞር ያለበት በወንድሞቹና በእህቶቹ ላይ ሳይሆን ሠራዊቱንና ኢትዮጵያን በትኖ ለመጥፋት ዝግጅት እያደረገ ባለዉ በጠላቱ በህወሓት ጥቂት ዘራፊ የሲቪልና ወታደራዊ መሪዎችላይ ነዉ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ሆይ!

የኛ ፍላጎት ፍትህ፣ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ የሰፉኑባት ኢትዮጵያ እዉን ሆና ማየት ነዉ። እርግጠኞች ነን የእናንተም ፍላጎት ከዚህ የተለየ አይደለም። እነዚህን እኛም አናንተም የምንፈልጋቸዉን እሴቶች ቀምቶን ሁለታችንንም እንደ ባሪያ ረግጦ የሚገዛን ዘረኛዉ የህወሓት/ኢህአዴግሥርዓት ነዉ። እናንተና እኛ ይህንን አንድ ላይ የሚረግጠንን ሥርዓት ጎን ለጎን ቆመን በጋራ መታገል ነዉ ያለብን እንጂ እርስ በርስ መተላለቅ የለብንም። ደግሞም ሁለት ፍትህ፣ ነፃነትና እኩልነት የናፈቃቸዉ ወንድማማቾች ነፃነታቸውን ቀምቶ የሚረግጣቸዉን ኃይል አንድ ላይ ሆነዉ ይፋለሙታል እንጂ እርስ በርስ አይተላለቁም። በዚህ የነጻነት ትግል ላይ የምንሳተፍ ወገኖችህ ወንድሞቻችንን በመግደል አናንተም እኛን ወንድሞቻችሁን በመግደል የሚገኝ ነገር ቢኖር ባርነትና የአገር አንድነት መፍረስ ብቻ ነዉ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አገሩንና ወገኖቹን የሚጠብቅ ኃይል ነዉ እንጂ ጠላቶቹ ግደል የሚል ትዕዛዝ በሰጡት ቁጥር በገዛ ወገኖቹ ላይ የሚተኩስ ኃይል አይደለም።

አንተ የኢትዮጵያ መለዮ ለባሽ ሆይ!

ዛሬ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በኮንሶ፣ በቤኒሻንጉልና ኦጋዴን ዉስጥ እህቶችህ “ወንድም ጋሼ” ድረስልን ብለዉ እየተጣሩ ነዉ፤ ወንድሞችህ “ጋሽዬ” አድነን እያሉህ ነዉ፤ አባትህና እናትህ “ልጄ አንተ እያለህ እንዴት እንዲህ ይደረጋል?” ብለዉ እየጮሁ ነዉ። መቼ ነዉ የምትደርስላቸዉ? መቼ ነዉ ከእስርና ከጥይት የምታድናቸዉ? መቼ ነዉ ተስፋ የምትሆናቸዉ?

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ፓሊስ አባላት ሆይ!

የህወሓት አገዛዝ ልትጠብቀው ከሚገባህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ደም እያቃባህ ነው፤ የውጭ ወራሪን ሳይሆን ፍትህ የናፈቀውን የገዛ ራስህን ወገን እንድትወጋ እያደረጉህ ነው፤ አገርህ ለጥቂቶች ብቻ የምትታለብ ጥገት ሆና ለማቆየት አንተን በመሣሪያነት እየተጠቀሙብህ ነው። የነፃነት ኃይሎች ትግል የገጠሙት ከህወሓት ዘራፊ ወታደራዊና ሲቪል መሪዎች ጋር እንጂ ከአንተ ጋር አይደለም። እነሱ ሁኔታው አላምር ሲል መሸሻ አዘጋጅተዋል፤ እድሜ ልካቸውን በልተው የማይጨርሱት ሀብት በውጭ አገራት አከማችተዋል። ያ ቀን ከመምጣቱ በፊት ግን አንተ የገዛ ወገንህን ገድለህ እንድትጨርስ፤ አሊያም በገዛ ወገንህ ተገድለህ እንድትጠፋ ይሻሉ። እንደምታውቀው በገባንበት ትግል አንተ ብቻ ተኳሽ፤ አንተ ብቻ ገዳይ አይደለህም። የነፃነት ኃይሎች ሊገላቸው የመጣን ኃይል ከመግደል አይመለሱም። በአሁን ሰዓት እንኳን ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የሠራዊቱ አባላት በነፃነት ኃይሎች ተጋድሎ መውደቃቸውን ታውቃለህ። ይህ መሆኑ ያሳዝነናል፤ ልትገድለን ስትመጣ ግን ባዶ እጃችንን አንጠብቅህም። እርስ በርስ የሚያጋድለን የህወሓት አገዛዝ ማብቃት አለበት። አንተ የዚህን እኩይ ስርዓት ትዕዛዝ አልቀበልም፤ ከድንበር መጠበቅ ውጭ የሀገሬን ህዝብ አልገልም ያልክ ቀን፤ ይህ ጦርነት ይቆማል። እንደልባቸው የሚያዙት ጦር እንደሌለ ሲያውቁ የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግር በጉልበት ሳይሆን በፖለቲካዊ መንገድ ለመፍታት ይገደዳሉ። ለነጻነትና ለእኩልነት እየተዋደቁ ያሉት ወገኖችህ ልክ እንዳንተ ይህ በአንድ ሀገር ህዝቦች መሀከል የሚደረግ ጦርነት እንዲቆም ይፈልጋሉ። በረሀ የገቡት ገበሬ ዘመዶችህ በሰላም አርሰው ልጆቻቸውን አሳድገው ጥሩ ዜጋ ማድረግ ይፈልጋሉ። መገደል፤ መታሰርና መሰቃየት ሰልችቶት በረሃ የገባው ወጣት ሀገሩ ሰላም ሆና፤ የነጻነት አየር እየተነፈሰ ትምህርቱን በነጻ አዕምሮ ተምሮ ለሀገሩ በጉልበቱና በእውቀቱ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚፈልግ እንጂ የጦርነት አባዜ ኖሮበት አይደለም በረሃ የወረደው። ስለዚህ ይህን ጦርነት ማስቆም የምትችለው አንተ ነህ። ይህን የምታደርገው ደግሞ እንዳንተ ሰላምና ነጻነት የሚፈልገውን ወገንህን በመግደል ሳይሆን አንተንም መላው ህዝቡንም አዋርደው መግዛት የሚፈልጉትን ጥቂት ዘራፊዎች እምቢ ማለት ስትችል ነው።

ከዛሬ ጀምሮ የተገኘውን ሁሉ አጋጣሚ ተጠቅመህ ሥርዓቱን በመክዳት የነፃነት ኃይሎችን ተቀላቀል። የሕዝብ ወገኖችን እንድትወጋ ስትታዘዝ እንድትወጋቸው ከተላክባቸው የነጻነትና የእኩልነት ታጋዮች ጋር ተቀላቀል። በአገኘኅው አጋጣሚ ሁሉ በግልም በቡድን መሣሪያህን ወደጥጋበኛ ህወሓት አዛዦችህ አዙር።

በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ከነፃነት ኃይሎች ጋር የሚቀላቀሉ የሠራዊቱ አባላት የክብር አቀባበል ይደረጋል። ሠራዊቱን የሚቀበሉ የሚያስተናግዱ፣ የሚያቋቁሙ ቡድኖችን በየቦታው አደራጅተናል። ሕዝብ በህወሓት አገዛዝ ላይ እንጂ በአንተ በሠራዊቱ አባል ላይ የያዘው ቂም የለም። እንዲያውም አንተ ራስህ ትግሉን እንድትቀላቀል ይፈልጋል። በሕዝብና በአገር ላይ በደል ሲፈጽም የኖረው የህወሓት አገዛዝ ፍፃሜለማፍጠን በሚደረገው ትግል የአንተ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

በኢትዮጵያችን ውስጥ እንዲኖር የምንፈልገው ሠራዊት ታማኝነቱ ለፓርቲ ሳይሆን ለሀገር የሆነ፤ ድንበሯን ከጠላት የሚከላከል፤ በሀገር ፍቅር ስሜት የነደደ፤ ሕዝብ የሚወደውና የሚያከብረው ሠራዊት ነው። ይህ ሠራዊት የሚገነባው በአንተው ነው። የህወሓት ወንበዴዎች ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሠራዊቱን የመበተን ዓላማም ሆነ ፍላጎት ያላቸው የነፃነት ኃይሎች የሉም። እነኝህ ብልሹ መሪዎቹ ተወግደውለት መዋቅሩ እንደተጠበቀ፤ ሹመትና የደሞዝ ጭማሪ በችሎታና ባደረገው አስተዋጽኦ ብቻ እንጂ ለአንድ ድርጅት ባለው ድጋፍ ወይም በዘውግ ማንነቱ ያልሆነ፤ ሙያውና ተጋድሎው ሀገሩን ከጠላት መጠበቅና የህዝቡን ደህንነት ማረጋገጥ የሆነ፤ በተልዕኮ ላይ ቢሰዋ ህዝቡ እንደጀግና የሚቀብረው፤ አካለ ስንኩል ቢሆን ህዝቡ በአክብሮት እስከ እድሜ ልኩ የሚጦረው፤ መለዮ ለብሶ በህዝቡ ውስጥ ሲገኝ ወጣቱ እንደሱ ለመሆን የሚመኘው አኩሪ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሆኖ እንዲቀጥል ነው ፍላጎታችን። ይህ ምኞት እንዲሳካ ግን ዛሬ የምትፈጽፈው ተግባር ወሳኝ ነው።

ውድ የአገሬ መለዮ ለባሾች፤

ለዴሞክራሲ ሲሉ እየታገሉ በሞቱትና አሁንም በሚታገሉት የሕዝብ ኃይሎች ስም የማቀርብላችሁን ጥሪ አድምጡኝ። ነፃ ሊያወጣችሁ እየታገለ ባለ ሕዝብ ላይ ፈጽሞ አትተኩሱ። ሕዝብ ላይ መተኮስ ማለት፤ የነፃነት ታጋዮች ላይ መተኮስ ማለት፤ በገዛ ራሳችሁ ላይ መተኮስ ማለት እንደሆነ እወቁ። ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው እንዴት በገዛ ራሱ ጭንቅላት ላይ ይተኩሳል? የእስከዛሬው በቅቶን ከእንግዲህ መንገዳችሁን አስተካክሉ። ከቻላችሁ ይህን የባርነት አዋጅ ለማስፈጸም ስንል ከሕዝብ ጋር አንዋጋም ብላችሁ በኅብረት ቆማችሁ ይህንን ጦርነት አስቁማችሁ ሀገሪቱን ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ለመውሰድ ታገሉ። ይህን ካልቻላችሁ የሕዝብን ትግል ተቀላቀሉ። በግልም ይሁን በቡድን መሠሪ የህወሓት ጄኔራሎችና አለቆቻችሁን በማስወገድ የጀግንነት ታሪክ ሥሩ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ፓሊስ አባላት ሆይ!

የኛ ፍላጎት ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያ እዉን ሆና ማየት ነዉ። የእናንተም ፍላጎት ከዚህ የተለየ አይደለም። ከሕዝብ ጎን ቁሙ፤ ሕዝብ በጎናችሁ ይቆማል።

ኢትዮጵያ አገራችን በክብር ለዘላለም ትኑር!