Wednesday, 6 January 2016

የአርበኞች ግንቦት 7 የትግል ጥሪ በራሪ ወረቀቶች በአርሲ ....

ኢሳት (ታህሳስ 27 ፥ 2008) የአርበኞች ግንቦት 7 የትግል ጥሪ በራሪ ወረቀቶች በአርሲ አሰላ ከተማ በርካታ ቀበሌዎች ትናንት ማክሰኞች በተሳካ ሁኔታ ለህዝብ መድረሳቸው ተገለጸ። በአካባቢው የሚኖሩ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አስተባባሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት በከተማው ውስጥ በብዙ ስፍራዎች ከ1600 በላይ የሚሆኑ የትግል ጥሪ ወረቀቶች በከተማዋ ለሚኖረው ህዝብ እንዲደርስ ተደርጓል። ሕዝብ በሚያዘወትርባቸው በተለያዩ ግልጽ ቦታዎች የትግል የጥሪ ወረቀቶች ተለጥፈው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። የተበተነውን የትግል ጥሪ ወረቀት የመንግስት የጸጥታ ሃይላት ለመሰብሰብ ሙከራ ቢያደርጉም፣ አብዛኞቹ የጥሪ ወረቀቶች በነዋሪው እጅ በመግባታቸው የጸጥታ ሃይል ሰራተኞች ያሰቡት ያክል ወረቀት ለመሰብሰብ እንዳልቻሉ ታውቋል። አብዛኞቹ ወረቀቶች ሰው ሊያያቸው በሚችልባቸው የተለያዩ ቦታዎች የተቀመጡ ሲሆኑ፣ ፖሊሶች ወረቀቶችን ለመሰብሰብ ሲጥር እንደነበር እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል። የመንግስት ጸጥታ ሃይሎች ለመሰብሰብ የቻሉት የትግል የጥሪ ወረቀት ከ50 እንደማይበልጥም ጉዳዩን በትኩረት ሲከታተሉ የነበሩ አስተባባሪዎች ከአሰላ ለኢሳት ተናግረዋል። ህብረትሰቡ የትግል ጥሪ ወረቀቱን በጉጉት እያነበበ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል። ከዚህ በፊት በአሰላ አካባቢ የትግል ጥሪ ወረቀት ተበትኖ ስለማያውቅ፣ ህዝቡ የትግል ጥሪ ሲደርሰው የግንቦት 7 አባላት በአካባቢው ይኖራሉ፣ ሊያደራጁንም ይችላሉ በሚል መንፈስ ደስተኛ መሆኑን የአካባቢውን ሰዎችን ያነጋገሩ አስተባባሪዎች ተናግረዋል። የህወሃት ኢህአዴግ የጸጥታ ሃይላትም፣ የደህንነትና የጸጥታ አካላት በምስጢር ይህን ያክል ወረቀት ሲበተን አለመድረሳችን  መዋረዳችንን ያመለክታል በማለት በቁጭት ሲናገሩ እንደነበር እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል። የተበተነው ወረቀት ላይ የሰፈረው “የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ኦሮሞ፣ አማራ፣ ጉራጌ፣ ትግሬ ብለን ሳንከፋፈል በአንድነት እንነሳ፣ የታሰሩት ይፈቱ” የሚል መልዕክት እንደነበረው አስተባባሪዎቹ አስታውቀዋል። መልዕክቱም በአማርኛና በኦሮምኛ የተጻፈ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። በበራሪ ወረቀቱ ላይ የግንቦት ሰባት አርማ ያረፈበት እንደነበርም ታውቋል። የአርበኞች ግንቦት 7 ትን ለማስተዋወቅና በአገሪቱ በሁሉም ክፍሎች እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ፣ በየአካባቢው የትግል ጥሪ ወረቀት መበተናቸውንና አባላት ማደራጀታቸውን እንደሚቀጥሉበት አስተባባሪዎቹ ለኢሳት ገልጸዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትግል ጥሪ ያያዙ ወረቀቶች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተበተኑ ነው። የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት በባህርዳት፣ አርባምንጭ፣ አዲስ አበባና፣ ወላይታ ሶዶ ከተሞች ባለፉት ጥቂት ወራት ተመሳሳይ መልዕክት ያላቸውን በራሪ ወረቀቶች ለህዝቡ ማድረሳቸው መዘገባችን የታወሳል።

http://ethsat.com/amharic/%e1%89%a0%e1%8a%a0%e1%88%b0%e1%88%8b-%e1%8a%a8%e1%89%b0%e1%88%9b-%e1%8b%a8%e1%8c%8d%e1%8a%95%e1%89%a6%e1%89%b5-%e1%88%b0%e1%89%a3%e1%89%b5-%e1%8b%a8%e1%89%b5%e1%8c%8d%e1%88%8d-%e1%8c%a5%e1%88%aa/

No comments:

Post a Comment