ኢሳት (ታህሳት 29 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ በሚገኙ ስድስት ክልሎች ጉዳትን እያደረሰ ባለው የድርቅ አደጋ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ የቤት እንስሳት በረሃብ ምክንያት መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጠ።
በዚሁ የድርቅ አደጋ ወደ ሁለት ሚሊዮን የቤት እንስሳት ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በህይወት የመቆየት እድላቸውም አደጋ ውስጥ መሆኑን ድርጅቱ በድርቁ ዙሪያ ባወጣው ረፖርት አመልክቷ።
ድርቁ ከፍተኛ ጉዳት ባስከተለባቸው የአማራ፣ ኦሮሚያ እና የደቡብ ክልሎች የሚገኙ በርካታ ወረዳዎች 75 በመቶ የሚሆነው የእርሻ ሰብላቸውን ማጣታቸውንም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ማስተባበሪያ ማዕከል ገልጿል።
ከወራት በፊት በተከሰተው የድርቅ አደጋ በቤት እንስሳት ላይ ከሚደርሰው ጉዳት በተጨማሪ በርካታ ተረጂዎች ለክፉኛ የአካልና የጤና ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነም ታውቋል።
በተያዘው የፈረንጆች አመት 15 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ በምዕራብና ምስራቅ ሃረርጌ የሚገኙ ዞኖች በድርቁ ሳቢያ እየደረሰባቸው ያለው የከፋ ችልግር ወደአራተኛ ደረጃ ከፍ ማለቱንንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
የፀጥታ ስጋቶች፣ ትራንስፖርትና የውሃ እጥረት የእርዳታ ስራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችልም ድርጅቱ ገልጿል።
ይሁንና የትኞቹ አካባቢዎች የፀጥታ ስጋት ሊሆኑ እንደሚችሉ ድርጅቱ ዝርዝር መረጃን ከመግለጽ የተቆጠበ ሲሆን በድርቁ ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶችም መዘጋታቸውን አመልክቷል።
በአሁኑ ወቅት የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ወቅታዊ እርዳታ እየቀረበላቸው እንዳልሆነም ታውቋል።
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው የአለም አቀፍ ማህበረሰብ በቂ ምላሽን ባለመስጠቱ ምክንያት የተረጂዎች ቁጥር ማሻቀቡንና ድርቁ መጠኑን እያሰፋ መምጣቱን ገልጸዋል።
የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ለሶስት ወር የሚሆን የእህል ክምችት በሃገር ውስጥ መኖሩን ሰሞኑን ማሳወቃቸው ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment