Wednesday, 5 April 2017

‹‹የዐማራ ገበሬዎች ተጋድሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም ምክንያት ሆኗል›› IRIN

ብራና ሬዲዮ - Branna Radio፤ መቀመጫውን በስዊዘርላንድ ያደረገው የተባበሩት መንግሥታት የተቀናጀ የዜና አውታር (IRIN) በዐማራ ገበሬዎች ተጋድሎ ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ ይዞ ወጥቷል፡፡ የዜና አውታሩ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው የዐማራ ገበሬዎች ተጋድሎ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አራት ወራት መራዘም ብቸኛ ምክንያት መሆኑን በዝርዝር ያስረዳል፡፡ መጋቢት 3 ቀን 2009 ዓ.ም የታተመው የኢሪን ዘገባ በጎንደርና በባሕር ዳር አስጎብኝ ግለሰቦችን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ የመንግሥት ኃላፊዎችንና የተለያዩ ዜጎችን እንዲሁም በአሜሪካ የተለያዩ ዪንቨርሲቲዎች ተመራማሪዎችንና የኢትዮጵያን ተወላጆች በማነጋገር የሰበሰበው መረጃ እንደሚያመለክተው ገዥው ቡድን በከተማ ያለውን አመጽ የተቆጣጠረው ቢሆንም በገጠር ያለው የዐማራ ታጣቂዎች የእግር እሳት ሆነውበታል ብሏል፡፡ 
የወልቃይት የዐማራ የማንነት ጥያቄ እስካልተመለሰ ድረስ የዐማራ ተጋድሎ ተዋናኝ ገበሬዎች መቼም ቢሆን ትግላቸውን እንደማያቆሙ በየቦታው ያነጋገራቸው ዜጎች በአጽንኦት አስረድተዋል፡፡ ከ20 ሺህ በላይ ወጣቶች ታስረው የስቃይ ሰለባ ቢሆኑም እንዲሁም በብዙ ቦታዎች ያለው አመጽ የቆመ ቢመስልም በሰሜን የዐማራ ገበሬዎች መራር የትጥቅ ትግል ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ እየሄደ ነው ይላል የኢሪን ዘገባ፡፡ 
በነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ባሕር ዳር በግፍ ወደ ትግራይ የተወሰደውን የወልቃይትን ሕዝብና መሬት ለማስመለስ ጩኸቱን ያሰማውን የዐማራ ሕዝብ የአገዛዙ ወታደሮች በጥይት ደብድበው ከ52 በላይ ሰዎችን ገደሉ፤ የዐማራ ተጋድሎ በተቀጣጠለባቸው ሳምንታት ብቻ ከ227 በላይ ዜጎች በጥይት ተገደሉ፤ ይህን ተከትሎም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ ይላል የዜና አውታሩ ዝርዝር ምልከታ፡፡ 
ይኼው የዜና አውታር በጎንደር ያሉ የሃይማኖት አባቶችንና ግለሰቦችን አናግሮ ‹‹በጎንደር ስለ አርበኛው ጎቤ መልኬና የወልቃይት የዐማራ ማንነት ጥያቄ አስተባባሪው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በፍቅርና በኩራት የማያወራ የለም፤ ገበሬዎች ለማንነታቸው ሕይወታቸውን ከመስጠት ወደ ኋላ አይሉም፤ ዐማራነት ካልተከበረ ወደ ኋላ የሚል የለም›› እንዳሉት በዳሰሳው አስፍሯል፡፡

ሙሉቀን ተስፋው
(ሙሉ የዜና አውታሩን ዘገባ ለመመልከት ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ማስፈንጠሪያ ይጫኑት
http://www.irinnews.org/analysis/2017/04/03/ethiopia-extends-emergency-old-antagonisms-fester

No comments:

Post a Comment