Tuesday, 27 October 2015
ብአዴን ወጪውን የሚሸፍነው በዋነኝነት ከነጋዴዎችና ከነዋሪዎች ነው
ጥቅምት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ብአዴን ወጪውን የሚሸፍነው በዋነኝነት ከነጋዴዎችና ከነዋሪዎች ነው። በርካታ የክልሉ ነጋዴዎች ገንዘብ እንዲለግሱ የጥሪ ወረቀት ደርሶአቸዋል። ድርጅቱ ከህወሃትና ከኦህዴድ ባላነሰ መልኩ በአሉን እንደሚያደርግ እየገለጸ ሲሆን፣ አገሪቱ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ አንዣቦባት ባለበት እንዲሁም የኑሮ ውድነቱ የህዝቡን ኑሮ ፈተና ውስጥ በጣለበት ሰአት ይህን ያክል ገንዘብ ህዝቡን አስገድዶ በማውጣት ለማክበር ማሰብ ኢ-ሞራላዊና ህዝብን መናቅ ነው ሲሉ መረጃውን የላኩ የብአዴን አባላት ተናግረዋል። ብአዴን እመራዋለሁ የሚለውን ህዝብ ማወረዱን የሚገልጹት አባላቱ፣ ህዝቡ በሰበብ አስባቡ መዋጮ እንዲያወጣ መደረጉ ለድህነት ከመዳረጉም በላይ እለታዊ ህይወቱን ለመምራት በማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ከህወሃት ጋር በሽርክና የተያዙት የብአዴን ኩባንያዎች ለአማራው ህዝብ የፈየዱለት ነገር እንደሌለ አባሎቹ አክለው ገልጸዋል። በተለይ ዋናዎቹ አመራሮች እንደፈለጉ የሚዘርፉት የጥረት ሃብት ፣ አንድም ቀን ሂሳቡ ተመርምሮ ለህዝብ ይፋ ሆኖ አያውቅም ይላሉ። የጥረት ሃብት የአማራ ህዝብ ሃብት ነው ይባላል እንጅ፣ ህዝቡ ስለሃብቱም የሚያውቀው እንደሌለ የሚገልጹት አባሎቹ፣ በዚህ ፈታኝ ወቅት ብአዴን በአሉን ከጥረት ሃብት በማውጣት በማክበር የነጋዴውንና የህዝቡን ስቃይ መቀነስ ይችል ነበር ሲሉ አስተያየታቸውን ደምድመዋል።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment