ፍርድ ቤቱ በተጠረጠሩት ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ላይ የ10 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ፈቀደ
- ፖሊስ ሌሎች ያልተያዙ አሉ ብሏል
ተጠርጥረው በተያዙት ሦስት ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ላይ የፌዴራሉ ፍርድ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ተጨማሪ የአሥር ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ፡፡
ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ካዋለችው የ‹‹ዞን ናይን›› ጦማሪያንና ጋዜጠኞች መካከል ስድስቱን በሁለት መዝገብ ከፍሎ ዛሬ ሚያዚያ 29 ቀን 2006 ዓ.ም. ለፌዴራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት አቅርቧል፡፡
በመጀመሪያው መዝገብ የቀረቡት የዞን ናይን አባላት የሆኑት ናትናኤል ፈለቀ፣ አጥናፍ ብርሃነና ኤዶም ካሣዬ ናቸው፡፡ በሁለተኛው መዝገብ የቀረቡት ደግሞ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስና ጦማሪ ዘለዓለም ክብረት ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የተመለከተው በዝግ ቢሆንም ከተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ለመረዳት እንደተቻለው፣ ጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ድርጅት ጋር በመገናኘት፣ ሥልጠና በመውሰድና ገንዘብ በመቀበል አገርና ሕዝብን ለማሸበር ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውን ፖሊስ ገልጿል፡፡ በተቀበሉት ገንዘብም ላፕቶፕና ሌሎች የጽሕፈት መሣሪያዎችን ገዝተዋል ብሏል፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሌሎች ያልተያዙ በመኖራቸው፣ ያልተተረጐሙ መረጃዎች እስኪተረጐሙና በሌሎች ምክንያቶች ተጨማሪ የ15 ቀናት ጊዜ ፖሊስ መጠየቁንና ፍርድ ቤቱ የአሥር ቀናት ተጨማሪ ጊዜ በሁለቱም መዝገቦች መፍቀዱን ከጠበቆች ለመረዳት ተችሏል፡፡
No comments:
Post a Comment