Tuesday, 1 April 2014

20 march 2014
                                                  
ከአዲስ አበባ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ!
ኢህአዴግ አገር የመምራት ብቃት እንደሌለው አዲስ አበባ ማሳያ ናት!!
ሌሎች አገሮች ለዋና ከተሞቻቸው ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የየአገሮቻቸው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ማሳያ በማድረግ አለም አቀፍ ተቋማትንና ጎብኝዎችን በመጋበዝ የከተሞቻቸውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደርጋሉ፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ግን በብዙዎች የአፍሪካ አገራት የአህጉሪቱ መዲና ተደርጋ የምትጠቀሰው አዲስ አበበባችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ኋላ አየተጎተተች ለኑሮ ምቹ ከሆኑ ከተሞች ምድብ መቀላቀለ ተስኗት ለነዋሪዎቿ የማትመች የፈተና ምድር ሆናለች፡፡
ኢህአዴግ ራሱን ልማታዊ መንግሥት በማድረግ ከሰየመበት ቅጽበት አንስቶ በልማት ሰበብ ዜጎች ከመኖሪያቸውና ቤተሰቦቻቸውን ከሚያስተዳድሩበት የንግድ ቦታ እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፡፡ በከተማይቱ እንዲነሱ የተደረጉት የንግድ ሱቆች በአብዛኛው በኪራይ ቤቶችና በቀበሌ ስም የተመዘገቡ በመሆናቸውም በሱቆቹ በመነገድ ይተዳደሩ የነበሩ ቤተሰቦች ባዶ አጃቸውን እንዲቀሩ ተደርገዋል፡፡
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለውን የመንገድ ዝርጋታ የተነሳ የተጠና ሥራ ባለመሰራቱ ከፍተኛ የህዝብ ገንዘብ የወጣባቸው መንገዶች ለምረቃ በበቁ በጥቂት ቀናት ልዩነት እንዲፈርሱ ተደርገዋል፡፡ የከተማው ነዋሪ ለሚጠቀምባቸው የመጓጓዣ አውታሮች ተለዋጭ መንገድ ባመዘጋጀቱም ለተጨማሪ ወጪ ተዳርጓል፡፡ ትራንስፖርት ማግኘት በሁሉም አካባቢዎች አስቸጋሪ በመሆኑ የከተማይቱ የሥራ እንቃስቃሴ ተዳክሟል፡፡ መንግሥት ‹‹የምትታለብ ላም›› በማለት የሚጠራው የኢትዮ ቴሌ ኮም አገልግሎት የለም የሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ጭምር በኢትዮጵ ቴሌኮም የተንቀራፈፈ አገልግሎተ የተነሳ ባንኮችና የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለደምበኞቻቸው ተገቢውን ግልጋሎተ ማበርከት አልቻሉም፡፡
የከተማይቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር የተወሰኑ ሠራተኞች ችግር እንደሆነ ተጠቁሞ ሠራተኞች ለስንብት ቢዳረጉም የኤሌክትሪክ መቆራረጥና ለረጅም ግዜ መጥፋት የከተማይቱ ኢንዱስትሪዎች ፤ንግድ ተቋማትንና ነዋሪውን እያማረረና ህይወቱን እያመሰቃቀለ ከመሄድ ውጭ ምንም አይነት ለውጥ አልታየበትም፡፡ በከተማይቱ ውሃ ማግኘት እንደ ትልቅ እድል መቆጠር ጀምሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የከተማይቱ 75% ነዋሪ ውሃ እንደሚያገኝ ቢናገሩም መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን በተቃራኒው ሆኗል፡፡ ጊዜያቸውን በትምሀርት ገበታቸው ላይ በመገኘት ማሳለፍ ይገባቸው የነበሩ ተማሪዎች ውሃ ለመቅዳት ረዥም መንገድ ለመጓዝ በመገደዳቸው የትምህርት ጊዜአቸው እየተበደለ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ ከተማይቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የከተማይቱ ነዋሪ ለሚገፋው አስቸጋሪ ህይወት ተጠያቂ ነው፡፡ ድርጅቱ አገሪቱን የመምራት ብቃት እንደሌለውም የወቅቱ የአዲስ አበባ ሁኔታ አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ የአዲስ አበባ ምክር ቤት የከተማይቱ ነዋሪ እየገፋው የሚገኘውን ፈታኝ ህይወት በማጥናት ህዝቡን በተለይም የከተማውን እና የዙሪያ አካባቢዋን ነዋሪ በማደራጀት በቅርቡ ‹‹የእሪታ ቀን›› በማለት ሰይሞ በ1ወር ጊዜ ውስጥ ሠላማዊ ሠልፍ ለማድረግ የወሰንን መሆኑን እየገለፅን የአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪዎች ሰላማዊ ሰልፉ በሚደረግበት ቀን በነቂስ በመውጣት በስርዓቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለመግለፅ እንዲዘጋጁ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

No comments:

Post a Comment