~ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ መፈታት አልነበረበትም
~የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የፓርላማ አባላት መቃወማቸው ጃዋር ፓርላማውን እንደተቆጣጠረው ያሳያል
~የኦሮሚያ የታችኛው መዋቅር ፈርሶ በቄሮ ተተክቷል፣
የፌደራል ጉዳዮች
የፖለቲካ ዘርፍ የጥር እና የካቲት 2010 ሪፖርት
መጋቢት 2010
መግቢያ
የፌዴራል ጉዳዮች ኢህአዴግ ወረዳ በጥር እና በየካቲት 2010 ዓ.ም ከወቅታዊ ጉዳዮች እና ማረጋጋት ጋር የተያያዙ ስራዎችን ሰርቷል፣ በየብሄራዊ ድርጅቱም ተመሳሳይ ስራዎች እና አደረጃጀቶችን የማጠናከር ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ እነዚህም እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
~በወቅታዊ ጉዳዮች እና ማረጋጋት ላይ የተሰሩ ስራዎች
በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ተካሄደ የመጀመሪያ ውይይት
የስብሰባው አጀንዳ፡-
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በታህሳስ 2010 ዓ.ም ያካሄደውን የ17 ቀናት ግምገማና ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች፣
የጓድ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ከስልጣን መልቀቅ ምክንያትና እንድምታው፣
አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአሁኑ ጊዜ ድጋሚ መታወጁ አስፈላጊነት የሚሉ ናቸው፡፡
ውይይቱን የመሩ ጓዶች፡-
ጓድ ሙሉጌታ ውለታው፣ እና
ጓድ ካይዳኪ ገዛሃኝ፡፡
በስብሰባው የተገኙ አባላት ብዛት፡- 64
ስብሰባው የተካሄደበት ቀን፡- 20/06/2010
(ግማሽ ቀን)
አካሄድ፡- በጓድ ሙሉጌታ ውለታው በሶስቱም ርእሰ-ጉዳዮች ላይ በቂ ዝግጅት የተደረገበት ዝርዝር ማብራሪያ ለአባላት (Presentation) ከቀረበ በኋላ አባላት ሃሳባቸውን በግልፅነት እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡
በርእሰ-ጉዳዮቹ ላይ የቀረቡ አስተያየቶችና የተነሱ ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
የጓድ ሃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን መልቀቅን በተመለከተ፡-
የስልጣን መልቀቅያ አስገቡ ሲባል መጀመሪያ ሁሉም አባል እንደተደናገጠ፣ እና ወደ ጭንቅንቅና ስጋት እንደገባ፣ ህዝቡ ውስጥም መደነጋገር እንደተፈጠረ፣ አስደናቂ ክስተት እንደነበር!
ሆኖም የተፈጠረውን ሃገራዊ ችግር በመፍታት ሂደት ጓድ ሃይለማሪያም ራሱን የመፍትሄ አካል ለመሆን ብሎ የወሰደው እርምጃ መሆኑን፣ እስኪፈቀድለት ስራውን እየሰራ የሚቆይ መሆኑን ተደጋጋሚ በሚዲያ ሲገለፅ መረጋጋት እንደተፈጠረ፣ ጓዱ የመፍትሄ አካል ለመሆን ከስልጣን መልቀቁ ተገቢ ነው፣ በፈቃደኝነት ስልጣን መልቀቁ በአዎንታ የሚታይ ታሪካዊ ውሳኔ ነው፣ ለሌሎቹ አመራሮችም ትምህርት የሚሰጥ፣ ለሌሎች ሀገራትም ጥሩ ተሞክሮ (Exemplary) ነው፣ በመልቀቁ አብዛኛው ጥሩ አስተያየት አለው፣
ነገር ግን እንዲለቅ ምክንያት የሆኑት ዝርዝር
ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
ሁለት ተቃራኒ አስተያየቶችም ተንፀባርቀዋል፡-
በአንድ በኩል የጓድ ሃይለማሪያም ብቃት ጥሩ ነው፣ ብዙ ስኬቶችን ልንጠቅስለት እንችላለን፣ ሆኖም ድክመቱ እርምጃ መውሰድ ላይ እንደሆነ፣ የዘገየ Resignation መሆኑ፣ በክብር መሸኘት እንደሚገባው፣
በሌላ በኩል ደግሞ የጓድ ሃይለማሪያም ከስልጣን መልቀቅ ጊዜው አይደለም፣ እንዲሁም የጓድ በረከትና የጓድ አባዱላ መልቀቅያ ተቀባይነት ያለማግኘቱና የጓድ ሃይለማሪያም መልቀቅያ ተቀባይነት ማግኘቱ Double Standard ነው፣ ሌላ ትርጉም ይኖረዋል፣
ጓድ ሃይለማሪያም ደካማ መሆኑ በኢህአዴግና በደኢህዴን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ተገምግሟል፣ በፈቃደኝነት ለቀቀ የተባለው ሽፋን ነው፣
በ17 ቀናት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የግምገማ መድረክ ላይ ለምን Resign አላደረገም? መጀመሪያ ተግባብተው ነበር ወይ? (ጥርጣሬ ይፈጥራል)፣
ለምን ሃይለማሪያም ብቻ ይለቃል? ካቢኔውስ ለምን አይጠየቅም? ምን ስር-ነቀል ለውጥ ይመጣል? የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የጓድ ሃይለማሪያምን የስልጣን መልቀቅያ ጥያቄ የተቀበለው በቀናነት (Genuinely) ነው ወይ? የ4ቱ ብሄራዊ ድርጅቶች አመራሮች አምነውበታል?
የኢህአዴግ ም/ቤት የስልጣን መልቀቅ ጥያቄው ባይቀበለውስ?
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድጋሚ መታወጁ ያለው አስፈላጊነትን በተመለከተ፡-
በአሁኑ ጊዜ የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ትክክል መሆኑ፣ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፣ ሻዕብያ ኢትዮጵያን ለመበታተን እየተረባረበ ነው፣ ኢህአዴግ ከመበታተን አድኖናል፣
ነገር ግን አዋጁ በትክክል ይተገበራል ወይ? ደንቢ ደሎ፣ ነቀምት፣ ጎንደር እየተጣሰ አይደለም ወይ? የህግ የበላይነት እየተሸረሸረ ነው፣
የመጀመሪያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት አልነበረበትም፣ አሁንም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጎን ለጎን መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ስራዎች መሰራት አለባቸው፣
ሆኖም በአዋጁ ላይ ለህዝቡን ማስረዳት አለብን፣ ስለ አዋጁ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ለጋዜጠኞች በቂ ዕድል አልተሰጠም፣ጥቂት ጥያቄዎች ብቻ ናቸው የተስተናገዱት፣
አዋጁ በፓርላማ እንዳይፀድቅ የሚደረግ ጥረት መኖሩን፣ የፓርላማ አባላት አዋጁን እንዳያፀድቁት ጫና መፍጠርና ማስፈራራት እንዳለ፣ የፓርላማ አመራሮች መስራት እንዳለባቸው፣ በዚህ ዙሪያ ላይ ካድሬው የራሱን ላፊነት እየተወጣ እንዳልሆነ፣
መከላከያ ከክልላችን ይውጣ የሚለው ህዝቡ ላይ ሆን አመራሩ እንደሆነ፣
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ግምገማና አቅጣጫዎችን በተመለከተ፡-
ኢህአዴግ እንዴት እየገመገመ ነው? የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ታህሳስ ወር ያካሄደውን ግምገማ እንደጨረሰ በወቅቱ ማብራሪያ ተሰጥቶ ነበር፣ ሆኖም ችግሩን በትክክል ለይተው ፈትተውት ነበር ወይ?
በየብሄራዊ ድርጅቱ የተካሄዱ ግምገማዎች የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባስቀመጠው አቅጣጫ እየሄዱ ነበር ወይ? በአሁን ዚዜ ከተለመደው የኢህአዴግ ባህሪ ውጭ የስልጣን ቅስቀሳ እየተካሄደ ነው፣ አመራሮቻችን አንድ ላይ ሆነው እየመሩን ነው ወይ?
ችግር ለድርጅታችን አዲስ አይደለም፣ አሁን ግን አመራሩ ፅናት ይጎድለዋል፣ ችግር የመፍታት ብቃት ያንሰዋል፣ ድርጅቱ አባላትን እያገኘ እየመራ አይደለም፣ የመረጃ ምንጫችን Facebook ነው፣ ፊት ሆነን ቀድመን እየመራን ስላልሆነ ሁኔታው ቀድሞን ሊያጠፋን ይችላል፣
የአባዱላ ከአፈ-ጉባኤነት መውጣትና መመለስ ለአባላት ግልፅ አይደለም፣
ለህዝቡ የሚሰጡት መግለጫዎች ህዝቡን እያደነባበሩት ናቸው፡፡
ኢህአዴግ ደካማ ድርጅት ነው ቢባልም እንኳ ጠቃሚ ድርጅት ነው፣
የኦሮሚያ የታችኛው መዋቅር ፈርሶ በቄሮ ተተክቷል፣
የብሄራዊ ድርጅት ዋሻ ካልፈረሰ መፍትሄ አይመጣም፣ ሕብረ-ብሄራዊ ፈዴራል ስርዓቱ አሳታፊ በሆነ መልኩ ይፈተሸ፣
የኦሮሚያ የቋንቋ ጥያቄም ተወያይቶ መልስ ለምን አይሰጥበትም? ቢፈቀድስ ምን ችግር አለው?
እስረኞች አፈታት ላይ ችግር አለ፣ ሰውን የገደሉ ወንጀለኞች ተለቀዋል፣ ከመስፈርቱ ውጭ ተፈፅሟል (ምሳሌ ኮሎኔል ደመቀ)፣
መሆን አለበት ተብሎ የተጠቆሙ ጉዳዮች፡-
ከምንም ጊዜ በላይ ልንረባረብ ይገባል፣ አመራሮቻችን አንድ ላይ ሆናችሁ ምሩን፣
መንግስት ከማንም ጊዜ በላይ ጠንካራ መሆን አለበት፣
የድርጅት መዋቅሩ/አባሉ ቀድሞ መወያየት አለበት፣ ከእኛ ምን ይጠበቃል በሚለው ላይ አተኩረን ተደራጅተን መታገል፣ መቀናጀትና በፅናት መጋፈጥ፣ እና Proactively መስራት ያስፈልገናል፣
የሚዲያ መግለጫዎች ጥንቃቄ ይደረግባቸው፣ የስልጣን ሽሚያ የሚመስሉ ገለፃዎች እየተላለፉ ናቸው፣
ማጠቃለያ፡-
ከፍ ብሎ በተዘረዘሩት አስተያየቶችና ጥያቄዎች ላይ በአባላትና በመድረኩ መሪዎች ላይ ሰፊ ማብራርያ ከተሰጠ በኋላ ልዩነት ሳይኖር የጋራ መግባባት በመፍጠር ተጠቃልሏል፡፡
በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ ውይይት
የስብሰባው አጀንዳ፡- ወቅታዊ ሁኔታ ያለበት ደረጃና የአባላት ስምሪት፣
ውይይቱን የመሩ ጓዶች፡-
ጓድ ነጋ አደሬ፣ እና
ጓድ ፀጋብርሃን ታደሰ፡፡
በስብሰባው የተገኙ አባላት ብዛት፡- ወንድ 75፣ ሴት 13፣ ድምር 88፡፡ በተለያየ ስራ ምክንያት በስብሰባው ያልተገኙ አባላት ብዛት 50 ናቸው፡፡
ስብሰባው የተካሄደበት ቀን፡- 28/06/2010 (ግማሽ ቀን)
አካሄድ፡- በፌዴራል ዞን አመራር በ26/06/2010 ዓ.ም በወቅታዊ ሁነታና የአባላትን ስምሪት አስመልክቶ የተሰጠውን ማብራሪያና ኦሬንቴሽን መሰረት በማድረግ በጓድ ነጋ አደሬ ዝርዝር ማብራሪያ ለአባላት ቀርቧል፡፡ በማብራርያው ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች፣
(ሀ) ወቅታዊ ሁኔታ ያለበት ደረጃ
በአሁኑ ጊዜ በሃገራችን እየተካሄደ ያለው ዓመፅ የቀለም አብዮት መሆኑን፣ የሃገራችን ፀጥታ ሁኔታ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን፣
የጠላት ግምገማ መላ ሃገሪቱ በቁጥጥሩ ስር ማድረጉንና አዲስ አበባን በመክበብ፣ ማንኛውም ነገር እንዳይገባ በመዝጋት ህዝቡ እንዲቸገርና ከውስጥ ዓመፅ እንዲነሳ በማድረግ ለመጨረሻ ጊዜ መንግስት ማፍረስ ይቻላል የሚል መሆኑን፣
ሆኖም እተካሄደ ያለው ዓመፅ በተደራጀና በሰለጠነ ሃይል የሚመራ ሳይሆን ከውጭ በሚሰጥ ትእዛዝ የሚፈፀም መሆኑን፣
የቀለም አብዮቱን እየመሩና እያቀጣጠሉ ያሉት ሃይሎች አክራሪው ኒዮ ሊበራል ሃይል፣ ሻዕብያ፣ ግብፅ፣ ፅንፈኛው ዳያስፖራ መሆናቸው፣
በአገር ውስጥ በኦሮሚያ ጥቂት ወጣቶች ለገንዘብ ብለው በእነዚህ ሃይሎች በሚሰጥ ትእዛዝ አማካኝነት የቀለም አብዮቱ አቀጣጣዮች ሆነው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው፣ ሆኖም አብዛኛው ወጣት በእነዚህ ወጣቶች ስር የተደራጀ ሳይሆን ዓመፅ በሚቀሰቀስበት ጊዜ በስሜታዊነት የሚከተላቸው መሆኑን፣ ህዝቡ ግን ሰላም የሚፈልግ መሆኑን፣
ሃገሪቱ ከገባችበት የፀጥታ አደጋ ለመታደግ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ትግል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን፣ አዋጁ መላ ሃገሪቱን የሚሸፍን ሆኖ ነገር ግን በሁሉም አካባቢዎች እኩል ክብደት እንደማይኖረው፣
ጠላት የቀለም አብዮቱን ለማሳካት የርብርብ ማዕከል ያደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ እንዳይሆን ማድረግ እንደሆነ፣ በዚህ ምክንያትም በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል በሁሉም አካባቢዎች የንግድና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መዘጋቱን፣ አዲስ አበባም ከአራቱ አቅጣጫዎች የግብርናም ይሁን የፋብሪካ ምርት እንዳይገባ በመዝጋት የፍጆታ ዕቃዎች እጥረት እንዲከሰትና ከዚህ በመነሳት ከውስጥ ዓመፅ እንዲነሳ ርብርብ እየተደረገ ነው፣
(ለ) በአሁኑ ጊዜ የሚኖረን ተልዕኮ
በአሁኑ ሰዓት ሃገሪቱ በቀለም አብዮት አማካኝነት ካጋጠማት አደጋ ለማውጣት በየተቋሞቻችንና በመኖሪያ አካባቢ ከአበባ በአዲስ ጋር በመቀናጀት የሚሰሩ ስራዎች አሉ፡፡ ማዕከል የምናደርገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መተግበር ሲሆን ትኩረታችንም ፀጥታን ማስከበር/ማስጠበቅ ነው፡፡ በዚህ መሰረት
በየተቋሙ የሚሰሩ
አባሉና ሲቪል ሰራተኛ በየተቋሙ መደበኛ የመንግስትን ስራ በጥብቅ እንዲፈፅም፣ አገልግሎት ምንም ምክንያት እንዳይቋረጥ ማድረግ፣ ፌስ ቡክና ሌሎችን አሉቧልታዎች እያዳመጠ ከስራ ውጭ እንዳይሆን ማድረግ፣ ጥብቅ ቁጥጥር መካሄድ ይገባል፣
አንዳንድ ሰራተኞች የቀለም አብዮቱን አራማጆችና መልእክተኞች ሊሆኑ ስለሚችሉ ሆን ብለው Sabotage ሊፈፅሙ ይችላሉ፣ ይህንን በጥብቅ መከታተልና ተፈፅሞ ሲገኝም መቆጣጠር ይገባል፣
ከዚህ በፊት የነበሩ አደረጃጀቶች (የስራ ሂደት ፎረም፣ የለውጥ ቡድን/1-ለ5 አደረጃጀት፣ የስራ ሂደት ፎረምና ሌሎችም አደረጃጀቶች) የበለጠ ውይይትና መግባባት የሚፈጠርባቸው በማድረግ ለሰላምና ለሕገ-መንግስት እንዲቆሙ ማድረግ ይገባል፣
በየተቋሙ በወቅታዊ ሁኔታ ላይ የጠቅላላ ሰራተኞች መድረክ በመፍጠር ማወያየትና በቂ ግንዛቤ ይዘው ለሰላም እንዲቆሙና መደበኛ ስራቸውን በጥብቅ እንዲያከናውኑ ማድረግ እንደሚገባ፣ አባላት ግንባር ቀደም ሆኖው መስራት እንደሚገባቸው የሚሉ በዝርዝር ቀርበው መግባባት ተደርሶባቸዋል፡፡
በመኖሪያ ሰፈር የሚሰሩ ስራዎች
በአዲስ አበባ ደረጃ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅም ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን፣
ሁሉም አባል ከዛሬ ጀምሮ ወደ መኖሪያ ሰፈር ወረዳ በመሄድ ሪፖርት ማድረግ እንደሚገባ፣ ከወረዳው በሚሰጥ ተልዕኮ መሰረት አብሮ መስራት እንደሚገባ፣ አዋጁን ለመጣስ የሚሞከሩ ሙከራዎችን በመከታተል ማክሸፍና ሪፖርት ማድረግ እንደሚገባ፣
ከኦሮሚያ ጋር የሚዋሰኑ የአዲስ አበባ ወረዳዎች የሚኖሩ አባሎቻችን ደግሞ ከኦሮሚያ ጋር ቅንጅት በመፍጠር በጋራ መስራትና የመረጃ ልውውጥ ማድረግ እንዳለባቸው፣ የሚሉትን በማቅረብ ውይይት ተካሂዶ መግባባት ተፈጥሯል፡፡
(ሐ) በውይይቱ ከአባላት የተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች
ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ተደጋግሞ ስብሰባ መጠራቱ ጥሩ ነው፣ አሁን ችግሩ ሁላችንም ያጠፋናል፣ ስለሆነም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈፀም እንሰራልን፣
አሁን ህዝቡ የመብራትና ውሃ ጥያቄ እያነሳ አይደለም፣ በሂወት የመቆየት የሰላም ጥያቄ ነው እያነሳ ያለው፣
ነገር ግን የተገመገመ ተጨባጭ ውጤት ጠብቀን ነብር፡፡ ኢህአዴግን ወክሎ ፓርላማ ውስጥ ያለው አባል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መቃወሙ በጁሃር ጎራ የተሰለፈ መሆኑን ያረጋግጣል፣ ይህ ጉዳይ ተገምግሞ ከኢህአዴግ የወጣ ጎራ ነው መባል ነበረበት፡፡ ስንታገል ማን ከማን ጋር ተሰለፈ በማለት በግልፅ ለይተን መሆን አለበት፡፡ ከኢህአዴግ አቋም መውጣት ማዕከላዊነትን መጣስ ነው፣ ማዕከላዊነትን መጣስ አያስጠይቅም ወይ? በዚህ ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አስፈላጊነትን በተመለከተ በዝርዝር ተወያይተን ስምምነት ላይ ደርሰን ነበር፣ አዋጁ ወደ ምክር ቤት ሲቀርብ የኦህዴድ አባላት መቃወማቸው ሰላምን አይፈልጉም ወይ? በፓርላማው ውስጥ የተፈጠረ ልዩነት የኦህዴድ አቋም ነው ወይ (በግልፅ ይቅረብልን)?
በኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ሁከት አስመልክቶ የኦህዴድ አመራር መግለጫና ማብራሪያ ለምን አይሰጥም? ለምን ሁሉም ነገር ለፀጥታው ሃይልና ኮማንድ ፖስት ይተዋል? የኦህዴድ ካድሬ ለምን ሱቆች እንዲከፈቱ አያደርግም? ካድሬው አሰላለፉ ከማን ጋር ነው፣ የት ነው ያለው? ለምን ኦሮሚያ ውስጥ የመንግስት መስሪያ ቤት ይዘጋል? ለምን አይጠየቅም? ይህ ኦሬንቴሽን ለኦሮሚያ ካድሬዎችም እየተሰጠ ነው ወይ? የኦህዴድ አባላት ምን እየሰሩ ናቸው? ከማን ጋር ሆነን ነው የምንታገለው?
የቀለም አብዮት እየተካሄደ ነው ብለን ከዚህ በፊት ደጋግመን ገልፀን ተቀባይነት አላገኘም ነበር፣ አሁን ተቀባይነት ማግኘቱ ጥሩ ነው፣ ግን አሁን የቀለም አብዮት አራማጅ ራሱ የኢህአዴግ አባል ነው፣ ችግርን መፍታት አቅቶናል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ስለምንኖር አሁን በአዲስ አበባ መስተዳድር ውስጥ ያለው አባል የፖለቲካ ቁመናው ወርዷል፣ ጎጠኝነትና ጠባብነት የተስፋፋበት ነው፣ የፌስ ቡክ ወሬ አቀባባይ በአጠቃላ አባላችን ነው፣
የመንግስት ሚዲያ የቀለም አብዮትን ማጋለጥ ሲገባው አሁንም የመልካም አስተዳደር ችግር እያለ ያወራል፣ ሰላም በሌለበት የመልካም አስተዳደር ችግር ለፈታ አይችልም፣ ህዝቡም ጥያቄው የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈታለ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ህዝቡ ሳይፈልግ ስራ እንዲያቆም እየተገደደ ነው፣ ሱቅ ለመክፈትና ስራውን ለመስራት ዋስትና አጥቷል፡፡
የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ እየተቀዛቀዘ ነው፣ ስብሰባ ነው፣ ወዘተ እየተባለ ቁጥጥርም እየላላ ነው፡፡ ችግር እየፈጠረ ያለው አመራር ነው፣ ወንጀለኞችን እየለየ መያዝና መጠየቅ አይፈልግም፣ ሰራተኛ እንዲቀዛቀዝ የሚያደርገውም ይህ ነው፣
መንገድና ንግድ እየተዘጋ እስከ መቼ ልንቀጥል ነው? ኢትዮጵያ እንደ ቴሌቭዥን የምትዘጋና የምትከፈት ሃገር መሆን የለባትም፣
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ በታህሳስ 2010 ዓ.ም ለ17 ቀናት ባካሄደው ግምገማ መተማመን ተፈጥሮ ነበር ወይ? ከሰማይ በታች ያለውን ሁሉ አንስተን ተወያይተናል፣ ተግባብተናል ብለው መግለጫ ከሰጡ በኋላ ለምን እንደገና ችግር ተፈጠረ? ለምን በመርህ መመራት አቃተን? ወዘተ… የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው በቂ ማብራርያ ከተሰጠ በኋላ የጋራ አቋም በመያዝ በየክፍለ ከተመማና ወረዳ በመሄድ ለመስራትም ስምምነት ተፈጥሯል፡፡
ሌሎች ስራዎች
ከፍ ብሎ ከተገለፀው በተጨማሪ ባለፌት ሁለት ወራት የሚከተሉት ስራዎችም ተሰርተዋል፡፡
የአዲስ ራእይ የመጨረሻው እትም በቁጥር 100 በመግዛት ለአባላት ተሰራጭቷል፣
በአዲስ ራዕይ መፅሄት የወጣው ‘ኒዮ-ሊበራሊዝም ሸሸ ወይስ አፈገፈገ’ የሚለው ርእሰ ጉዳይ አጠር ብሎ ተዘጋጅቶ በወረዳ ደረጃ ውይይት ተካሂዶበታል፣ ቀጥሎም በህዋስ ደረጃ ውይይት ተካሂዶበታል፣
በየተቋሙ የመንግስት ሰራተኞችን በመሰብሰብ በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
No comments:
Post a Comment