የግንባሩ የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የኦሮሞ ህዝብ በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም የሚያስከበር አዋጅ መደንገጉ ለድርጅቱ ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ ያስገኝለታል በሚል በኢህአዴግ የፖሊሲ፣ ጥናትና ምርምር ተቋም የቀረበው ምክር እንዳልሰራ በመታመኑ ፣ ሰነዱ በኦሮምያ ክልል በየደረጃው ባሉ አካላት ውይይት ተካሂዶበት፣ የድጋፍ ሰልፍ እንዲደረግለት ልዩ ትዕዛዝ ተላልፏል። በአቶ በረከትና አባይ ጸሃዬ የሚመራው የምርምር ተቋም፣ የአዲስ አበባን ስም መቀየር እንዲሁም የተጠቃሚነት መብታቸውን ማወጁ ዳር እስከዳር በሰልፍና በፈረስ ድምቀት የፈጥራል የሚል ምክር ለግሶ ነበር። ከአዋጁ በሁዋላ የተደረገው ግምገማ ግን አዋጁ በተቃራኒው በተቀናቃኝ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንድ ዝምድናን በማንገሱ እንዲሁ ሌሎች ተጨማሪ ጥያቄዎችን በማስነሳቱ፣ ኢህአዴግ በሙሉ ሃይሉ ተጠቅሞ የድጋፍ ሰልፎች እንዲደረጉና ፖለቲካዊ ኪሳራውን እንዲሸፈን ጥብቅ ትእዛዝ ሰጥቷል። ብአዴን በበኩሉ “ከኦሮሞ ህዝብ ድጋፍ መታጣቱን የተመለከቱ የህወሃት የማህበራዊ ምንደኞች፣ አማራን በማነሳሳት አማራና ኦሮሞን ለማጋጨት የሚያደረጉትን ጥረት ኢህአዴግ ያስታግስልኝ” ሲል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህወሃት ደጋፊ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በአማራ ክልል ፕሬዚዳንትና ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ላይ የጀመሩትን የስድብ ዘመቻ አንስቶ ለኢህአዴግ አቅርቧል። በስብሰባው ላይ በህወሃትና በብአዴን መካከል ያለው ክፍተት እየሰፋ መሄዱን ምንጮች ገልጸዋል። ብአዴን በክልሉ ፕሬዚዳንት ላይ በማህበራዊ ሚዲያ የተከተፈተውን ዘመቻ ህወሃት የሚመራ ነው ብሎ ያምናል። ህወሃት በበኩሉ ግለሰቦች የራሳቸውን ሃሳብ የመሰንዘር መብት እንዳላቸው በመግልጽ፣ ሃላፊነቱን ከራሱ ለማሸሽ ይሞክራል። ብአዴን፣ በኦሮምያና አማራ አካባቢዎች የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ህወሃት እየተዳከመ የመጣውን የመሪነት ቦታውን መልሶ ለመያዝ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ባሰማራቸው አባሎቹ አማካኝነት አንዱ ህዝብ የሌላው ጠላት እንደሆነ አድርጎ እያቀረበ የኦህዴድን ድጋፍ በመያዝ ብአዴንን ለማዳከም እየሞከረ ነው በማለት ወቀሳ ሲያቀርብ፣ ህወሃት በበኩሉ በአማራ ክልል ጸረ ህወሃት አቋም እንዲጸባረቅና ህወሃት የከፈለውን መስዋትነት በመካድ ፣ ህወሃት በአማራ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው የተወሰኑ የብአዴን አመራሮች ውስጥ ለውስጥ ስራዎችን እየሰሩ ነው ብሎ ያምናል። ለጊዜው አንዱ በሌላው ላይ አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ባይፈቅዱም፣ በብአዴን እና በህወሃት መካከል የሚታየው ልዩነት እየሰፋ እንጅ እየጠበበ እንደማይሄድ ምንጮች ይናገራሉ። ህወሃት ኦህዴድን በመያዝ የህወሃትን የበላይነት በሚቀናቀኑ የተወሰኑ የብአዴን መሪዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድና ድርጅቱን መልሶ በስሩ ለማድረግ የሚጠቀምበት ስልት ሊሳካ መቻልና አለመቻሉ በኦህዴድ አቋም ይወሰናል የሚሉት እነዚሁ ምንጮች፣ ብአዴን የህሃት ካድሬዎች በአማራና ኦሮሞ መካከል ችግር ለመፍጠር እየሰሩና ይቁምልኝ ከማለት ውጭ፣ ከኦህዴድ ጋር የተለዬ ግንኙነት ሲመሰረት አይታይም ይላሉ። የኦሮሞ ህዝብ አዲስ የወጣውን የአዲስ አበባ አዋጅ ውድቅ ማድረጉ በብአዴኖች ዘንድ ውስጥ ለውስጥ ደስታን ሳይፈጥር እንዳልቀረም ምንጮቻችን ይገልጻሉ። አዋጁ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ቢያገኝ ኖሮ ህወሃት ቅደመ ሁኔታ የሌለበት ድጋፍ ( unconditional support) ከኦህዴድ በማግኘት ተጠናክሮ እንዲወጣና በብአዴን ላይ የፈለገውን እርምጃ ለመውሰድ እንዲያስችለው ያደርግ ነበር በማለት የብአዴን መሪዎችን በቅርብ የሚያውቁት ምንጮች ትንታኔያቸውን ያቀርባሉ። ሰሞኑን በባህርዳር ለ3 ቀናት የተካሄደው የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ስብሰባ በዋነኝነት በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ያለውን አለመተማመንና ጥርጣሬ ለማስወገድ ያለመ ነበር።
ኢሳት ዜና
Friday, 7 July 2017
ኢህአዴግ በሙሉ ሃይሉ ተጠቅሞ የድጋፍ ሰልፎች እንዲደረጉና ፖለቲካዊ ኪሳራውን እንዲሸፈን ጥብቅ ትእዛዝ ሰጥቷል
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment