ሰበር ዜና
*
ዘአቃቂ ቃሊቲ ጥምቀተ ባህር
*
ስማቸው ለጊዜው የማይገለጽ የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ በጸጥታ ሃይሎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተወስደው ባልታወቀ ስፍራ ለረጅም ሰአት እንዲቆዩ ከተደረገ በዋላ ማምሻ ላይ መለቀቃቸው ተሰማ፡፡ የአቃቂ ቃሊቲ ጥምቀተ ባህር ይዞታን ለማስከበር በተዋቀረው ኮሚቴ ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ ዘጠኙ አድባራት መካከል የአንዱ ደብር አለቃ የሆኑት ለጊዜው ስማቸው የማይገለጽ አባት በጠዋት ከቤታቸው በደህንነቶች ከተወሰዱ በዋላ ባልታወቀ ስፍራ ቀኑን ሙሉ እንዲቆዩ ተደርገው የተለያዩ ጥያቄዎች ሲቀርብላቸው ከዋለ በዋላ ዛቻና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ማምሻ ላይ ወደ መኖሪያቸው መመለሳቸውን የመረጃ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
የቤተክርስቲያን ይዞታ ተነጥቆ በድብቅም ካርታና ፕላን ወጥቶበት እየተገነባ ያለውን የእምነትን ቅድስናና የሃይማኖትን ክብር የሚያዋርድ ካፍቴሪያና የመዝናኛ ፕሮጀክትን ህዝቡና ቤተክርስቲያን በማውገዝና በመቃወም ጥንታዊውን መንፈሳዊ ይዞታ ለማስከበር በተዋቀረው ኮሚቴ ውስጥ አባል ሆነው የተጣለባቸውን ሰማያዊ አደራ በጽናት ሲወጡ የቆዩ አባቶችን በስልክ የተለያዩ ዛቻዎችና ማስጠንቀቂያዎች ሲደርሳቸው ቆይቶ አሁን የተወሰደው ርምጃ አባቶችን በማስፈራራትና በማስጨነቅ ህብረተሰቡ ግንባታውን እንዲቀበል እንዲያደርጉ ታሳቢ የሆነ መሆኑን ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡
"ከስፍራው ጋር የተያይዞ ለሚፈጠረው የትኛውም ችግር ተጠያቂ ናችሁ፡፡ ልማቱን እየተቃወማችሁ ነው፡፡" የሚል የክስና የማስፈራሪያ ዛቻ አባቶች ላይ እያቀረቡ ያሉት አካላት አባቶችን በማስጨነቅና በማስፈራራት እንዲሁም በመከፋፈል የቀረበውን ፍትሃዊ ጥያቄ ለማስቆም ከፍተኛ ጫና እያደረጉ መሆኑን ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ እየደረሰባቸው ያለውን ከፍተኛ ጫናና የማስጨነቅ ተግባር የደብር አለቆች ስለ ቤተክርስቲያን ሲሉ ለመናገር ፈቃደኛ ባይሆኑም ከተገለጸውም በላይ የተለያዩ መከራዎችን በጸጋ እየተቀበሉ እንዳለ ሁኔታውን በቅርበት የሚከታተሉ አካላት ይገልጻሉ፡፡
አንዳንድ ምንጮች እንደሚጠቁሙት ከሆነ አባቶችን በማስፈራራትና በማለያየት የጥምቀት በአል በየ አጥቢያው እንዲከበር ለማድረግ አደገኛ ተግባር እየተፈጸመ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ህዝቡ በጸሎት እንዲተጋና ከአባቶች ጎን እንዲቆምም ያሳስባሉ፡፡
ቤተክርስቲያን ይዞታዋን ለማስከበር በግልጽና ህጋዊ በሆነ መንገድ ጥያቄዋን እያቀረበች በምትገኝበት ወቅት ከኮሚቴ አባላት መካከል የይሁዳን ስራ የሚሰራን ሰው በማዘጋጀትና የስብሰባዎቹን ሂደት በሞባይል መቅረጸ ድምጽ ቀርጾ የሚያቀብልን ሰው መላክ ለምን አስፈለገ? ብለው የሚጠይቁት ታዛቢዎች የትኛውም አካል ቤተክርስቲያን በምታደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ መሳተፍ እየቻለ ቤተክርስቲያን እንደ ወንጀለኛ ተቆጥራ በውስጧ ሆነው የእጇን በረከት እየበሉ ነገር ግን ሰማያዊውን ህይወት ዘንግተው ወሬ የማቀበል ርካሽ ተግባር ላይ የተሰማሩ ምናምንቴ ሰዎችን መጠቀም ለምን አስፈለገ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ በዘመነ ስጋዌም በአምላካችን ለታላቅ ክብርና ስልጣን ከተመረጡት መካከል በሃዋርያት ጉባኤ መካከል የነበረው ይሁዳ አምላኩ ከሰጠው ታላቅ ክብርና ስጦታ ይልቅ ሰላሳ ብር በልጦበት አምላኩን ለመሸጥና የሃዋርያትን ጉባኤ ለመበትን በጀርባ ከአይሁድ ጋር ይደራደር እንደነበር እንዲሁ ዛሬም በቤተክርስቲያን ጉያ ተሸሽገው ቤተክርስቲያንን ለመሸጥ የሚያደቡ የሲኦል እጩዎች በመካከላችን መኖራቸውን የተስተዋለበት አጋጣሚ መኖሩን ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡
*
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቤተክርስቲያንን ጥያቄ ለበላይ የመንግስት አካላት በማቅረብና ይዞታውን ለማስከበር ከሁሉም ደብራት ከተዋቀሩት የኮሚቴ አባላት መካከል በቀዳሚነት ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ካሉት መሃል አራት የኮሚቴው አባላት በቅርቡ እንዲታሰሩ መወሰኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች ከታማኝ ምንጮች ተሰምቷል፡፡ ህግና ስርአት ባለበት ሀገር በጠራራ ፀሃይ በዘመናት ተከብሮ በቆየው ሃይማኖታዊ ይዞታ ላይ በመግባት በህገ መንግስቱ የተረጋገጠውን ህዝብ በሀገሩ በነጻነት ሃይማኖቱን የማራመድ መብቱን በመጣስ ህገወጥ ተግባር የፈጸሙ የክፍለ ከተማው ባለ ስልጣናት በህግ ሳይጠየቁ በነጻነት እየኖሩ "ጥንታዊው መንፈሳዊ የቤተክርስቲያን ይዞታ ባልተገባ መንገድ ተወስዷል፤ በስፍራውም እየተከናወነ ያለው ፕሮጀክት የሃይማኖትን ክብርና የእምነትን ቅድስና የሚያዋርድ ያልተገባ ስራ ነው፡፡" ብለው በግልፅ በስነ ሥርአት ጥያቄ ያቀረቡ ንጹሃንን ለማሰር መነሳት የበለጠ በህዝቡና በአስተዳደሩ መካከል መተማመንን የሚያጠፋና ህብረተሰቡንም የሚያስከፋ ጉዳዩን በሰከነ አግባብ በማየት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ውሳኔ ላለመወሰን የተያዘውን አቋም የሚያሳይ ነው፡፡
የሰላምና የፍቅር ቤት የሆነችው ቤተክርስቲያን አቤቱታዋንና ጥያቄዋን በሥርአትና በአግባብ ሃላፊነት በተሞላበትም መንገድ እያቀረበች ቢሆንም በክፍለ ከተማው እየተፈጸመ ያለው ተግባርም ሃላፊነት የጎደለው ለችግሩም ዘላቂ መፍትሄ የማያስገኝ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በህግና በአግባብ ለቤተክርስቲያኒቱ ጥያቄ ፍትሀዊ ምላሽን እንዲሰጡ ዛሬም ቤተክርስቲያን ተማጽኖዋን ታቀርባለች፡፡
*
ተጨማሪ ሰበር ዜና ስለደረሰን ከቆይታ በዋላ ይዘን እንመለሳለን፡፡
*
ቸር ወሬ ያሰማን!
*
"ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተክርስቲያን!"
Sunday, 20 December 2015
ዘአቃቂ ቃሊቲ ጥምቀተ ባህር
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment