Thursday, 5 March 2015

በጄኔቫ የሚገኘው የኢትዮጰያ ኤምባሲ “የተቃዋሚ ደጋፊዎች ናችሁ”ላላቸው ኢትዮጰያውያን ፓስፖርት አላድስም አለ።
የካቲት ፳፭(ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በስዊዘርላንድ የዙሪክ ነዋሪ የሆኑት አክቲቪስት ፊዮሬላ ሮማኖ ለኢሳት እንደገለጹት ፓስፖርታቸውን ለማሳደስ ቀጠሮ አስይዘው ከሚኖሩበት ዙሪክ ኤምባሲው ወደሚገኝበት ጀኔቫ የ3 ሰዓት መንገድ ተጉዘው ቢሄዱም፣ የኤምባሲ ስራተኞቹ በአካል ሲያዩዋቸው በተቃውሞ እንቅስቃሴ እንደሚሳተፉ ስለለዩዋቸው አገልግሎቱን ሳይሰጡ መልሰዋቸዋል።
ኤምባሲው እንደደረሱ ጎይቶም በሚባል ሰራተኛ የተሰጣቸውን ፎርም ከሞሉና ፎቶግራቸውን ከሰጡ በሁዋላ በስዊዘርላንድ ለምን ያህል ዓመት እንደቆዩ ጥያቄ የቀረበላቸው ወይዘሮ ፊዮሪና፤ ለ13 ዓመት መቆየታቸውን ሲናገሩ ፦” በ 13 ዓመታት ውስጥ ለሀገርዎ ምን ሰሩ?” የሚልና ከፓስፖርት እድሳቱ ጋር ተያያዥነት የሌለው ተጨማሪ ጥያቄ እንደቀረበላቸው ተናግረዋል።
ለቀረበላቸው ጥያቄ በደፈናው፦”እሱን ሀገሬ ስሄድ የማምንበትን ጉዳይ እፈጽማለሁ” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን የገለጹት ወይዘሮ ፊዮሪና፤ ይኽኔ ፦”አንቺን በደንብ እናውቅሻለን፤ ለጊዜው ፓስፖርት ማደስ አቁመናል” እንደሏቸው ገልጸዋል።
ቀጠሮ አስይዤ ደርሶ መልስ የ6 ፡00 ሰዓት መንገድ ተጉዘው ከመጡ በሁዋላ የዚህ ዓይነት ምላሽ በማግኘታቸው የተበሳጩት ወይዘሮ ፊዮሪና፤ በጊዜው ኤምባሲ ለመሄዳቸውና የፓስፖርት እድሳት ጥያቄ ለማቅረባቸው ማረጋገጫ ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው ቢጠይቁም ኤምባሲው በእምቢተኛነቱ መጽናቱን ገልጸዋል።
ጉዳዩን ለስዊዘርላንድ ፖሊስ ባመለከቱት መሰረትም የፖሊስ የማረጋገጫ ወረቀትና ፊርማ ይዘው መመለሳቸውን ተናግረዋል።
ይኽኔ፦”መንግስትን መቃወምም ሆነ መደገፍ መብት እስከሆነ ድረስ ከኤምባሲ አገልግሎት እንዳናገኝ ምክንያት ሊሆን አይችልም” ስላቸው ፦”እሱን ሄደሽ ኢሳት ላይ ተናገሪ” አሉኝ የሚሉት ወይዘሮ ፊዮሪና፤ በተቃውሞ ሰልፎች በመሳተፋቸውና የኢሳት ደጋፊ በመሆናቸው ከኤምባሲው አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውን በዝምታ እንደማያልፉት ተናግረዋል።
“እኔ ብቻ ሳልሆን በርካታ እንደኔ ያሉ ህጋዊ ነዋሪዎችም ተመሳሳይ ችግር እየደረሰባቸው ነው” ያሉት ወይዘሮ ፊዮሪና፤ ከሀገራችን ተሰደን እዚህም ሁለተኛ ስደተኛ መሆን ስለሌለብን የኔ ዓይነት ተመሳሳይ ችግር ከደረሰባቸው ወገኖቼ ጋር በመሰባሰብ በኤምባሲው ላይ ተከታዩን ህጋዊ እርምጃ ለማስወሰድ ተዘጋጅተናል ብለዋል።
ወይዘሮ ፊዮሪና ፦”ኤምባሲው ለኢትዮጰያውን በእኩልነት አገልግሎት መስጠት ካልቻለና የቤተሰብ ኩባንያ ከሆነ እኛ ባለንበት ሀገር ሊኖር አይገባም”ያሉት ወይዘሮ ፊዮሪና፤ ኢትዮጰያውያን ያለምንም ፍርሀት ተባብረን ልንነሳ ይገባል ብለዋል። ወይዘሮ ፊዮሪና ሀሳባቸውን ሲያጠቃልሉም ፦ እኔን ኢትዮጰያዊ ያደረገኝ ጥንት አያቶቼ የከፈሉት የደም መስዋእትነት እንጂ ትናንት የመጣ ወያኔ አይደለም “ብለዋል።

No comments:

Post a Comment