Wednesday, 31 December 2014

የደብረማርቆስ የመሰናዶ ተማሪዎች የመንግስትን ፖሊሲ ተቃወሙ
ተማሪዎች ኢህአዴግን እንዲመርጡ በሚል በግዳጅ በተዘጋጀው የፖለቲካ ስልጠና ላይ ተማሪዎች ፈታኝ የሆኑ ጥያቄዎችን አስተያየቶችን ሰጥተዋል ።
ኢህአዴግ እነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን የመሰሉ ሰዎችን አሸባሪዎች ማለቱ ትክክል አለመሆኑን የሚገልጹት ተማሪዎች፣ ኢህአዴግን የሚበልጡት በመሉ አሸባሪ እያለ እንደሚፈርጃቸው ተናግረዋል ( )
ፕ/ት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የሚኖርበት ቤት 400 ሺ ብር እንደሚከፈልበት የተናገሩት ተማሪዎች፣ አባይን መገደብ ያልቻለ መንግስት እንዴት ይህን ያክል ገንዘብ ይከፍላል ሲሉ ጠይቀዋል። ( ) 
በኮምቦልቻ ደግሞ መድረኩን የሚመሩት ባለስልጣን በውጭ አገር የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት ትክክለኛ መረጃ አያሰራጩም በማለት መናገራቸውን ተከትሎ ተማሪዎች በውጭ የሚገኙ ሚዲያዎች ከኢቲቪ ቀድመው መረጃ በመናገር ተአማኒነትን ማትረፋቸውን ለዚህም ደግሞ በየጊዜው የሚከዱ ባለስልጣናት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። አቶ በረከት ስምኦን የሂትለር የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበረው ጆሴፍ ጎብልስ፣ ውሸት ሲደጋጋም እውነት ይሆናል ያሉትን በተደጋጋሚ እንደሚናገሩና፣ ይህንኑ በኢቲቪ ላይ ተግባራዊ እያደረጉት መሆኑን ተማሪዎች መናገራቸውን መዘገባችን ይታወቃል።
የመለስ ዜናዊን ማረፍ መጀመሪያ የሰማነው ከውጭ ሚዲያዎች ነው፣ ኢቲቪ ዜናውን የነገረን ከ2 ወር በሁዋላ ዘገይቶ በማለት በውጭ ሚዲያዎችን ላይ የቀረበውን ትችት ተከላክለዋል። የመንግስት ባለስልጣናት በየጊዜው መክዳታቸው መረጃ ለማግኘት አስተዋጽኦ ማድረጉን የገለጹት ተማሪዎች፣ ኢሳት በጋዜጠኛ አበበ ቶላ ወይም አቤ ቶክቻው አማካኝነት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጋዜጠኞችን ህብረት ፕሬዚዳንትን ቃለ ምልልስ በማድረግ ያቀረበው ዘገባ፣ የመንግስት ባለስልጣናት እውነተኛ ፍላጎት የሚያሳይ ነው ሲሉ አክለዋል። ( )
በጋምቤላ በመዠንገር አካባቢ የደረሱ ጭፍጨፋዎችንና ሌሎችንም በርካታ የአገራችን ችግሮች የሰማነው በውጭ ሚዲያው በመሆኑ፣ በሚዲያው ላይ የሚቀርበው ወቀሳ ትክክል አይደለም ብለዋል።
የብሄር ግጭትን በተመለከተ ዋናው ተጠያቂው መንግስት ነው ያሉት ተማሪዎች፣ በተለይ የትግራይን ህዝብ ከአማራውና ከኦሮሞው ጋር ለማጋጨት የሚያደርገው እንቅስቃሴ በሁዋላ ላይ አገሪቱን ይጎዳታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ተማሪዎች ካነሱዋቸው ቅሬታዎች መካከል አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በስልጤ ወራቢ ተገኝተው ስለተናገሩት እና በቀይ ባህር ላይ ስላለቁት ኢትዮጵያውያን ይገኝበታል። አንድ ጠ/ሚኒስትር እንዴት የገዛ ዜጎችን ገረድ ብሎ ይሳደባል ሲሉ የጠየቁት ተማሪዎች፣ እንዲህ አይነት ንግግር እንኳንስ አገር ከሚመራ ከተራ ዜጋም አይጠበቅም በማለት ተችተዋል። መንግስት ለመለስ ዜናዊ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት በስርአት እንዲቀበሩ ማድረጉን ያስታወሱት ተማሪዎች፣ በቅርቡ ወደ የመን ሲሄዱ ላለቁ ከ70 በላይ ኢትዮጵያውያን ሌላው ቢቀር ሰንደቃላማ እንኳን ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ አለመደረጉ በዜጎች መካከል ያለውን ልዩነት የሚየሳይ ነው በማለት አክለዋል። ( )
የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አያያዝ በአገራችን ፍትህ እንደሌለ የሚያሳይ ነው በማለት የፍትህ ስርአቱን የተቹት የመሰናዶ ተማሪዎች፣ አቶ አንዳርጋቸው ከስድስት ወራት የእስር ጊዜ በሁዋላ፣ በቤተሰብና በጠበቃ እንዳይጎበኙ፣ የታሰሩበትም እንዳይታወቅ መደረጉ የፍትህ ስርአቱ በአገራችን መቀበሩን ያሳያል ብለዋል።


Source: ESAT

No comments:

Post a Comment