Monday, 18 September 2017

በወቅቱ የአገራችን ሁኔታ ላይ የአርበኞች ግንቦት 7 መግለጫ

መስከረም 6 2010
አገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው። ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በኢትዮጵያዊያን ላይ በተለያዩ ግንባሮች ጦርነት ከፍቷል።
በሰሜን ጎንደር ጭልጋ፣ መተማና ሽንፋ አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር ሰፍሮ ሕዝብን ለመፍጀት ትዕዛዝ እየተጠባበቀ ነው። የአማራና የቅማንት ተወላጆችን ለማጋጨት ሲሸረብ የነበረው ዱለታ የመጨረሻ ደረሻ ላይ ደርሷል። የህወሓት አገልጋይ መሆኑ በተደጋጋሚ ባረጋገጠው የምርጫ ቦርድ አስፈፃሚነት ይካሄዳል የሚባለው ሕዝበ ውሳኔ ግጭትን ከማስፋት በስተቀር የሚኖረው ጠቀሜታ የለም። ሕዝበ ውሳኔው በራሱ አስፈላጊ አልነበረም፤ ይደርግ ከተባለም ምርጫው ሊያስፈጽም የሚችል ተዓማኒን ተቋም የለም። የሕዝበ ውሳኔው ውጤት ከምዝገባው በፊት መገመት የሚቻል ቢሆንም ድምፆች ተገልብጠው የውሸት ውጤቶች ይፋ እንደሚሆኑ ከወዲሁ መናገር ይቻላል። ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ከተቋቋመ ጀምሮ አንዴም ተዓማኒነት ያለው ምርጫ አስፈጽሞ የማያውቅ በመሆኑ አሁን የተለየ ነገር ይፈጽማል ብሎ ተስፋ ማድረግ አይቻልም። የአማራ ክልልና የትግራይ ክልል ተፈራረሙ የሚባለው የድንበር ማካለል ጉዳይም ሌላው ተቀጣጣይ እሳት ነው። ይህ ስምምነት የብአዴን አመራሮች የህወሓት አገልጋይነታቸውን መሬት በይፋ በመስጠት ያረጋገጡበት ሰነድ ሆኖ በሕዝብ ልብ ተመዝግቧል። ለወልቃይትና ቅማንት ጥያቄዎች ፈጽሞ የተለያዩ ምላሾችን መስጠት በራሱ ጠብ ጫሪነት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሰሜን ጎንደርን በሶስት ዞኖች የመሸንሸን እቅድ አለ። ህወሓት አማራን በአጠቃላይ፤ በተለይ ደግሞ ጎንደርን ለማዳከም ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው።
በሶማሊ ክልል ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው። በጅጅጋ ከተማ እየተፈፀመ ያለው የዘር ምንጠራ የህወሓት አገዛዝ አገራችንን ወደየት እየወሰዳት እንደሆነ አመላካች ነው። የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ወገኖቻችን ከየቤታቸው እየታደኑ ከክልሉ እንዲወጡ ተደርገዋል፤ ተደብደበዋል፣ ተደፍረዋል፤ ንብረታቸው ተዘርፏል። ይህንን ዘርን የማጥራት ሥራ በበላይነት የሚመራው የሶማሊ ክልል ልዩ ጦር መሆኑ ሁኔታው ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል። “የሶማሊ ልዩ ጦር ምንድነው? የማነው? ለምንድነው የተቋቋመው?” የሚሉ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ይሻሉ። ወገኖቻችን ለሰቆቃ የሚዳረጉት በመታወቂያቸው ላይ የተፃፈው ብሄር እየታየ መሆኑ ለሶማሊ ብቻ ሳይሆን ለሌላውን የኢትዮጵያ ክፍል አስደንጋጭ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው። በሶማሊና በኦሮሚያ አዋሳኝ መንደሮችና ከተሞች እየተደረገ ባለው ከመደበኛ ጦርነት ያልተናነሰ ግጭት ሳቢያ የወገኖቻችን ሕይወት እየተቀሰፈ ነው፤ ይህን የሚፈጽመው ደግሞ የአገዛዙ አካል የሆነ ዘመናዊና ትጥቅና ስልጠና ያለው የጦር ሠራዊት ነው።
የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት አለ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ላይ አይደለም። ሆኖም፣ አርበኞች ግንቦት 7ን የሚያሳስበው ችግር የሐረር ከተማና ዙርያው ነዋሪ ሕዝብ ሰላምና ደህነት እንጂ የክልላዊው መንግሥት መኖር አለመኖር አይደለም፤ የክልሉ አስተዳደር ከመነሻው ጀምሮ ችግር ያለበት ነው። አሁን ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ በፊት ከነበረው ይለያል። ሐረር ከተማና ነዋሪዎቿ አደጋ ላይ ናቸው።
በግልብ ሲታይ ቅራኔው በአንድ በኩል ህወሓት፣ ሶህዴፓና ሐብሊ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ብአዴንና ኦህዴድ የተሰለፉ ይመስላሉ። ይህ ግን የተሳሳተ ምስል ነው። ብአዴንና ኦህዴድ ራሳቸው የህወሓት ስሬቶች ናቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በህወሓት አገዛዝ ምን ያህል የተማረረ መሆኑ እና ለውጥ የሚፈልግ መሆኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከታታይ በታዩ የተቃውሞ እንቅስቃሰዎች ገልጿል። የሙስሊም ወገኖቻችን ድምፃችን ይሰማ፤ የኦሮሚያ፣ የአማራና የኮንሶ የሕዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች እና በቅርቡ መላው አገሪቱን ያዳረሰው የግብር ማዕቀብ የኢትዮጵያ ሕዝብ በህወሓት አገዛዝ ምንያህል የተሰላቸ መሆኑን ገላጮች ናቸው። ህወሓት ከዚህ ቀውስ ለመውጣት የሕዝብን ጥያቄዎች ከመመለስ ይልቅ ሌሎች ቀውሶችን መፍጠር መርጧል። አሁን እያየነው ያለነው መተራመስ የዚህ እኩይ ውሳኔ ውጤት ነው። ህወሓት ራሱን ከአጣብቂኝ ለማውጣት መፍትሄ አድርጎ የወሰደው ሕዝብን ከሕዝብ አጋጭቶ ተጠያቂነትን ወደ ብአዴንና ኦህዴድ ማዞር ነው። በዚህም ምክንያት ህወሓት የጥፋት በትሩን የራሱ ስሪት በሆኑት ብአዴንና ኦህዴድ ላይ ሰንዝሯል፤ በሚቀጥሉት ሳምንታትና ወራት ውስጥ በእነዚህ ድርጅቶች መሪዎች ላይ የሚደርስ ህወሓታዊ ጥቃት እንደሚኖር መጠበቅ ብልህነት ነው።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አገራችን ያለችበት አሳሳቢ ሁኔታ ይገነዘባል። በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከህወሓት በሚወረወሩለት የማዘናጊያ አጀንዳዎች ከትግሉ ሳይናጠብ ሙሉ ትኩረቱን አገዛዙን የመቀየር ትግል ላይ እንዲያደርግ ያሳስባል።
በየቦታው እየፈነዳዱ ያሉ ችግሮች ሁሉ ምንጫቸው ህወሓት ነው። የችግሮቹ መፍትሄ ያለውን ህወሓትን ማስወገድና በምትኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታ ያገኘ መንግሥት ማቆም ነው። ይህን ለመፈፀም በዲሞክራሲያዊ ኃይሎች መካከል ሰፊ የሆነ ትብብር መፍጠር ያስፈልጋል። አርበኞች ግንቦት 7 ከኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር፣ ከአፋር ሕዝብ ፓርቲና የሲዳማ ሕዝብ ዲሞክራሲያን ንቅናቄ በጋራ ለመሥራት የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ (ኢአን) መፍጠሩ ይታወቃል፤ ከኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር ጋርም የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል። በእንዲህ ዓይነት ወቅት እነዚህ ስምነነቶች አገራችን ለማዳን ወሳኝ ናቸው። ሌሎች ድርጅቶችም እንዲቀላቀሉን ጥሪዓችንን እናቀርባለን።
የህወሓትን የስልጣን ዘመን እያበቃ ነው። አርበኞች ግንቦት 7 የሕዝብን ፀረ ህወሓት ሁለገብ ትግል እያስተባበረ ይገኛል። አርበኞች ግንቦት 7 በመላው ኢትዮጵያ በሕዝብ ጋር ሆኖ የህወሓት አገዛዝን እየተፋለመ መሆኑን ይገልፃል። ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ቆመን የምናደርገው ትግል ለፍሬ እንደሚበቃ ጥርጥር የለውም።
ብአዴንና ኦህዴድ ውስጥ ያሉ ልባም ወገኖች ዛሬ ከሕዝብ ትግል ጎን ቢቆሙ ራሳቸውን ከማዳን ባለፈ ለአገርና ለወገን መልካም እንደሠሩ ሊቆጠርላቸው እንደሚችል አለበለዚያ ግን ከአገዛዙ ጋር መጥፋታቸው የማይቀር መሆኑን እንዲገነዘቡ አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል። ስለሆነም ከህወሓት ጋር አብራችሁ ለራሳችሁም ለወገኖቻችሁም መከራና ሰቆቃ አትሸምቱ።
የወቅቱ የአገራችን ችግሮች የሚወገዱት ትግላችንን አቀናጅተን ህወሓትን ስናስወግድ ብቻ ነው። ይህንን ትግል በግባር ቀደምትነት ለመምራት አርበኞች ግንቦት 7 በፊት መስመር ተሰልፏል። በአንድነት ድል እናደርጋለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
አንድነት ኃይል ነው!

The Intercept የሚባለው ሚስጥር አውጪ ህውሃት በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስትን ሚስጥር ማስፈትለኩን ታወቀ

የአሜሪካንና የሌሎች መንግስታትን ድብቅና ከፍተኛ ሚስጥር በማጋለጥ የሚታወቀው ዘ ኢንተርሴፕት (The Intercept)የሚባለው ሚስጥር አውጪ (Whistle blower) በመስከረም 13 ቀን 2017 እኤአ ህውሃት በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስትን ሚስጥር ማስፈትለኩን ታወቀ።

ይህን በሃይለማርያም ደሳለኝ ቁንጮነት የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ጥብቅ ሚስጥርን ይዞ ወደ አደባባይ የወጣው በአሜሪካ መንግስት ተፈላጊ ከሆኑ ግለሰቦች መካከል በቀዳሚነት የተሰለፈው የቀድሞው የስለላ አባል የሆነው ኤድዋርድ ስኖውደን (Edward Snowden)እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
ኤድዋርድ ስኖውደን በአሜሪካ መንግስት በከፍተኛ ሚስጥርነት የተያዙትን መረጃዎች ለዊክሊክስ በማስተላለፉ ምክንያት በሩሲያ የጥገኝነት ህይወት እየመራ እንደሚገኝ ይታወቃል።
የአሜሪካ መንግስት በስልጣን ላይ ካለው የህውሃት አገዛዝ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ምድር እያደረገ ያለውን ከፍተኛ የስለላ ሚስጥር መረጃ ዘ ኢንተርሴፕት (The Intercept) በተባለው የሚስጥር አውጪ ሊጋለጥ መቻሉን ለመረዳት ተችሏል።
ዘ ኢንተርሴፕት (The Intercept) ይህን ጥብቅ መረጃ ያገኘው ከኤድዋርድ ስኖውደን የሚስጥር ፋይል እንደሆነም ገልጿል።
በመንግስታቶች የሚከናወኑ ከፍተኛ ሚስጥሮችን (classified information) በማጋለጥ የሚታወቀው ዘ ኢንተርሴፕት(The Intercept) በመስከረም 13 ቀን 2017እኤአ ለህትመት ባወጣው ዶክመንት የአሜሪካው የስለላ አካል የሆነው NSA (National Security Agency) ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር በምስራቅ አፍሪቃ ግዙፍ የስለላ ተቋም መገንባቱ በማስረጃ ለአለም አሳውቋል።
ይህ ዘመናዊ መሆኑ የተነገረለት የስለላ ተቋም ኢትዮጵያኖችን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪቃ የሚገኙ አጎራባች አገራት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴዎች እንዲሁም የሚያደርጉትን የስልክና የኢንተርኔት ንግግሮች ወይም ግንኙነቶች በመጥለፍ የስለላ ተግባሩን እንደሚያከናውን ዘ ኢንተርሴፕት(The Intercept) አጋልጧል።
NSA (National Security Agency) በመባል የሚታወቀው የአሜሪካ የስለላ ተቋም የኢትዮጵያ መንግስት ላበረከተለት የቦታ እና የሰው ሃይል ስጦታ ውለታን በውለታ ለመመለስ የአምባገነኑን የኢትዮጵያ ሃይሎችን በኤሌትሮኒክ ሰለላ (electronic surveillance) ስለጠና መስጠቱ በዶክመንቱ ተጋልጧል::
የኢትዮጵያ መንግስት የኤሌክትሮንክስ የስለላን ዘዴ የተጠቀመበት ሽብርተኝነትን ወይንም ደግሞ ወንጀልን ለመዋጋት ሳይሆን የገዛ ዜጋውን ወይም ህዝቡን ለማሰቃየት እንደሆነ ዘ ኢንተርሴፕት (The Intercept) ከፍተኛ የሆኑ የሰብአዊ መብት ተመራማሪ የሆኑትን Mr. Felix ጠቅሶ ዘግቧል።
የአሜሪካው National Security Agency በየካቲት 2002እኤአ በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያውን የአንበሳ ኩራት (Lion’s Pride) ተብሎ የሚጠራውን የስለላ ማዕከል ማቋቋሙን ይህ ዶክመንት ይጠቁማል።
ይህ የስለላ ማዕከል እንደተቋቋመ ቀለል ያለ ሚሽን (ተልእኮ) የሚመሩ አስራ ሁለት ኢትዮጵያውያኖች ብቻ እንደነበሩትም ተዘግቧል።
ነገር ግን በ2005እኤአ ይህ ቁጥር በሚያስገርም ሁኔታ አድጎ ስምንት የአሜሪካ ወታደራዊ ፕርሶኔል እና መቶ ሶስት ኢትዮጵያዊያኖች ተሰማርተው እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ማዕከሉ ወደ አርባ ስድስት የሚሆኑ የስራ ቦታዎች እንደነበሩት ይሄው ዶክመንት አያይዞ ገልጧል።
ዘ ኢንተርሴፕት ያወጣው ሚስጥራዊው ዶክመንት እንደሚጠቁመው የአሜሪካው የስለላ አካል የሆነው NSA አዲስ አበባ ከሚገኘው የስለላ ማእከሉ በተጨማሪ በድሬዳዋም በ2006እኤአ ሁለተኛውን የሰለላ ተቋም መዘረጋቱን ለማወቅ ተችሏል።
በድሬዳዋ የተቋቋመው የስለላ ማዕከል በህዝቦች መካከል የሚደረገውን ግንኙነት በተለይ ደግሞ በሶማልያ፣ ሱዳን እና በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚደረጉ ማንኛውንም የኤሌክትሮኒክ ግንኙነትን ወይም ንግግርን የሚያዳምጥ መሆኑን ይሄው ዶክመንት አስፍሯል።
በሌላ በኩል ደግሞ የአሜሪካ መንግስት እና የኢትዮጵያ መንግስት በመተባብር በኡጋዴንና በሶማሊያ ጠረፍ እካባቢ የሚደረገውን የህዝቦች ግንኙነት የድሬዳዋውን ማዕከል በመጠቀም መሰለላቸውን ሚስጥራዊው ማስረጃ ያትታል።
የጥቁር ኩራት ወይም Lion’s pride ተብሎ የሚጠራው የስለላ ማዕከል በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተመሰረቱት ማዕከላት በተጨማሪ በጎንደር አካባቢም ሶስተኛ ማዕከል መከፈቱን የኢንተርሴፕት Intercept የምርምር ዶክሜንት ጨምሮ ገልጧል።
የአሜሪካ የስለላ ድርጅት በዑጋዴን አካባቢ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመሰለል የኢትዮጵያ መንግስት በንጹሃን ዜጎች ላይ ለፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ተባባሪ መሆኑ እጅግ በጣም አስነዋሪ ነው በማለት የሰብአዊ መብት ተመራማሪ የሆኑት Mr. Horne ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ዘ ኢንተርሴፕት the Intercept ባወጣው በዚህ ዶክመንት በአሁኑ ሰአት እነዚህ ከአሁን በፊት በአዲስ አበባ ፣ በድሬዳዋ እንዲሁም በጎንደር የተከፈቱት የስለላ ማእከላት መዘጋታቸውን የሚያሳይ ምንም ማስረጃ እንዳላገኘ ዘግቧል።
አያይዞም የአሜሪካ መንግስት ከዚህ አሳፋሪ እና ህገወጥ ድርጊቱ መቆጠብ ይኖርበታል ሲል አሳስቧል።