ነኅሴ ፳፭ (ሀያ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ነሃሴ 19 ቀን በኦሮምያ ክልል በቡሌሆራ ከተማ፣ በ1949 የተገነባውን የገበያ ማእከል በማፍረስ የመኪና መናሃሪያ ለማድረግ፣ እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት ህዝቡ ያሰማውን ተቃውሞ ተከትሎ ፖሊሶች በወሰዱት እርምጃ ከ150 በላይ ሰዎች በድብደባ ሲቆስሉ፣ ወገኖ ወንዳቸው የተባለ ወጣት በጥይት ተመትቶ ሆስፒታል ገብቶ እየታከመ ነው። የከተማው ባለስልጣናት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ሳይስማሙና ለነጋዴዎቹ አስፈላጊውን ካሳ ሳይከፍሉ የማፍረሻ መኪኖችን በመያዝ ማፍረስ መጀመራቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ህዝቡ ድርጊቱን እንዳየ በባለስልጣኖቹ ላይ ድንጋይ በመወርወር ተቃውሞውን ገልጿል። ፖሊሶች ተኩስ በመክፈት ህዝቡን ለመበተን ሙከራ ቢያደርጉም፣ ግጭቱ ለሰአታት ቆይቷል። በፖሊስ ዱላና ጥይት የቆሰሉት በአንቡላንስ እየተጫኑ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። ይህንን ተከትሎ ፖሊሶች እስከ ሌሊት ድረስ ወደ መኖሪያ ቤቶች እየገቡ ነፍሰጡሮችን ሳይቀር ደብድበዋል። በእለቱ 26 ሰዎች ሲታሰሩ፣ 13 ተለቀው፣ 13 ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። አቶ ታደለ ቢቂላ የተባሉ አባት ልጃቸው ታደለ ቢቂላ ክፉኛ መደብደቡን ተከትሎ ወደ ሆስፒታል ሲሄዱ፣ ልጄን ፖሊስ ደብድቦብኝ ነው ብለው በመናገራቸው የተባሱጩት ፖሊሶች እርሳቸውንም ከ13ቱ ተከሳሾች መካከል በመቀላቀል ፍርድ ቤት አቅርበዋቸዋል። የዞኑ የሰማያዊ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ ጌታቸው በቀለ፣ ፖሊስ የወሰደውን እርምጃ አውግዘዋል። ለተጎዱት ቤተሰቦች አስቸኳይ ካሳ እንዲከፈላቸው አቶ ጌታቸው ጠይቀዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ከምርጫው በሁዋላ ከ2 ሺ ያላነሱ የኦሮሞ ተወላጆች መታሰራቸውን የምስራቅ አፍሪካ የሰብአዊ መብት ሊግ ገልጿል። ሊጉ ባወጣው መግለጫ በቡሌ ሆራ፣ ደምቢ ዶሎ፣ ምእራብና ሰሜን ሸዋ ዞን አፈሳው ተጧጡፏል። በዋራ ጃርሶ ወረዳ ከ400 በላይ አርሶአደሮች አመጽያንን አስጠግታችሁዋል በሚል መታሰራቸውን አስታውቓል። ከታሰሩት መካካል የ20 ሰዎችን ስም ይፋ አድርጓል።
No comments:
Post a Comment