Wednesday, 25 February 2015

ኢትዮጵያ ውስጥ ዳኛ ቢኖር

ኢትዮጵያ ውስጥ ዳኛ ቢኖር – ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

Prof. Mesfin
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም
የጎረቤት ኬንያ ዳኛ ለኬንያ መንግሥት አስፈጻሚው ክፍል ልኩን ነገረው፤ ሕገ መንግሥቱን በመርፌ አስተኝተህ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር ሕግ ለማውጣት አትችልም፤ ስለዚህም የሰነዘርኸውን የጉልበት ሕግ አንሣ፤ አለው፤ ዳኛ አይጥፋ! ሌላ ቢቀር ከጎረቤት ዳኝነትን እንስማ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ዳኛ ቢኖር ስንት ጋዜጠኛ፣ ስንት የሃይማኖትና ስንት የፖሊቲካ መሪዎች ከየወህኒ ቤቱ ይወጡ ነበር! ሁላችንም እንደልባችን ሳንፈራ፣ ሳንፈራራ በሙሉ ነጻነት ችግሮቻችንን የወያኔን ጭቆና ጨምሮ ለመወያየትና መፍትሔዎችን ለመለዋወጥ የምንችልበት መድረክ፣ ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ ራድዮና ቴሌቪዥን በኢትዮጵያ ውስጥ ይኖረን ነበር፤ ስንት ሰው ሥራ ያገኝ ነበር፡፡
ከሁሉም በላይ በየመንገዱ ጠመንጃ የያዘ ሊያስፈራራን የሚሞክር ሆድአደር እያየን፣ እንደዚሁም በየጫካው ያሉትን እያሰብን ሰላማችንን ከምናጣ አበባውን ትተን፣ ሩዙን ትተን፣ የተወደደልንን ጤፋችንን እያመረትን አዲስ ኑሮ ብንጀምር የተሻለ ነበር፡፡
ግን አንድ እንቅፋት አለብን፤ እነዚህ ከየኪዮስኩ እውቀት ገዝተን አዋቂዎች ሆነናል የሚሉት እንትኖች እንመጀመሪያ ችግሩ እንዲገባቸው፣ ሁለተኛ መፍትሔው እንዲገባቸው፣ ሦስተኛ ጉልበትና እውቀት አንድ አለመሆናቸውን ብቻ ሳይሆን በጉልበት እውቀት የማይገኝ መሆኑን ማሳመን በረዶ እየወረደ የስሜን ተራራን መውጣት ነው፤ በረዶ ሳይኖር ወጥቼዋለሁ!
እነዚህን የጉልበት አዋቂዎች — ስለሽማጌሌዎችና አሮጊቶች ሳያስቡ፣ ስለመብራት ኃይል ሳያስቡ፣ ስለውሀ ሳያስቡ ሁሉም በጉልበት ፎቅ ይውጣ የሚሉ! ይባስ ብለው ለእስረኛውም ፎቅ እየሠሩለት ውጣ! ሊሉት ነው!
እነዚህ የጉልበት አዋቂዎች የአበሻ ኑሮ፣ ቡናው፣ ሙቀጫው፣ ምጣዱ፣ በርበሬው፣ ቁሌቱ፣ ቄጤማው፣ ዶሮና በግ ማረዱ፣ ኧረ ስንቱ! ሳይገባቸው ቻይና በነገራቸው የሚያውቁትን የሚረሱ ማን ያስተምራቸው! እናውቃለን ስለሚሉ እንዴትስ ይማራለ? በእውነት ለመማር ቢፈልጉስ ስንት ዓመት ሊያስፈልጋቸው ነው! እግዚአብሔር እንሱንም እኛንም በምሕረቱ ይጎብኘን! የሚያስተምር ጎረቤት አያሳጣን!
source: satenaw

No comments:

Post a Comment