Friday, 5 September 2014

• የከተማ አውቶቡስ ድርጅት 80 አውቶቡሶችን አቅርቧል
• ‹‹ምኒልክ ለኢትዮጵያ ምንም ካላበረከቱ ለምን ከእሳቸው ዘመን ጀምረን ዘመናዊ ኢትዮጵያ ብለን እንጠራለን?›› ሰልጣኞቹ
• ኦነግ በትግሉ ወቅት አልነበረም መባሉ በኦህዴድ ካድሬዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከነሃሴ 27 ጀምረው በየ ትምህርት ቤቱ በፕላዝማ ስልጠና ጀምረዋል፡፡ ስልጠናውን በበላይነት የሚመራው የኢህአዴግ ጽ/ቤት መሆኑ ታውቋል፡፡ ሰልጣኞቹን ለማመላለስ ከአንበሳ የከተማ አውቶቡስ 80 አውቶቡሶችን ጠይቆ መውሰዱን ድርጅት ሰራተኛ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ የተለያዩ የኢህአዴግ አደረጃጀቶችን የወከሉ ካድሬዎችን ጨምሮ የሀይማኖት አባቶችም የሚገኙበት ሲሆን ለስልጠናው አበልን ጨምሮ፣ የከተማ አውቶቡስ፣ ትምህርት ቤትና ሌሎች የህዝብ ገንዘብ እየወጣ እንደሚገኝ ሰልጣኞቹ ገልጸዋል፡፡
በፕላዝማ የሚሰጠው ስልጠና በታሪክ ላይ ያተኮረ ሲሆን በተለይም አጼ ምኒልክ ከፍተኛ ጥፋት እንደፈጸሙና ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ይህ ነው የሚባል አስተዋጽኦ እንዳላበረከቱ መገለጹ ታውቋል፡፡ በተቃራኒው የኢህአዴግ አባላት ሳይቀሩ ‹‹በታሪክ አዲሲቱ ወይንም ዘመናዊ ኢትዮጵያ ብለን የምንማረው ከምኒልክ ዘመን ጀምሮ ያለውን ነው፡፡ ምኒልክ ምንም ካላበረከቱ ለምን ከእሳቸው ዘመን ጀምረን ዘመናዊ ኢትዮጵያ እያልን እንጠራለን?›› የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ገዥው ፓርቲ አሸባሪ ብሎ የሚጠራቸውን ጨምሮ በሰላማዊ መንገድ የሚቃወሙት ፓርቲዎችም ወቀሳ የቀረበባቸው ሲሆን ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ተገልጾአል፡፡
ስልጠናው ላይ ሌሎች ፓርቲዎች የኢህአዴግን ያህል አስተዋጽኦ እንደሌላቸው በስፋት የተገለጸ ሲሆን ለአብነት ያህልም ‹‹ኦነግ ትግሉ ላይ አልነበረም›› መባሉ በኦህዴድ ካድሬዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ አንድ ስልጠናው ላይ የሚገኝና ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የኦህዴድ ካድሬ ‹‹የኢህአዴግን ታሪክ ለማግነን ሲባል የምናውቀውን ታሪክ ሁሉ እየካዱ ነው፡፡ ምንም አይነት የትግል ስልት ይከተል ረዥም የትግል ታሪክ ያለውን ድርጅት ትግሉ ላይ አልነበረም በማለት ከትዝብት ውጭ የሚያስገኘው ውጤት አይኖርም፡፡ የኦህዴድ አባል ብሆንም በመዋሸት ኦነግን ልታገለው አልችልም፡፡ ይህ ጉዳይ የመወያያ ርዕስ ሆኖ መቀረቡም የሚያስገርም ነው፡፡›› ሲል ሁኔታውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡

No comments:

Post a Comment